ሠላምን ዘላቂ ለማድረግ ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ እሴቶችን መጠበቅ እንደሚገባ ተመለከተ

72

አሶሳ ፤ ሚያዚያ 02 / 2013( ኢዜአ)፡-በሀገሪቱ ሠላምን ዘላቂነት ለማድረግ የእምነት እና ባህል እሴቶችን መጠበቅ ላይ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ተመለከተ፡፡

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የባህል ፌስቲቫል በአሶሳ ከተማ እየተከበረ ነው፡፡

ከፌስቲቫሉ ተሳታፊዎች መካከል አቶ ዚያድ አብዱላሂ እንዳሉተ አሁን ለሚታየው ግጭት የእምነትና ባህል እሴቶች  እየተሸረሸሩ መምጣት አንዱ ምክንያት ነው፡፡

ወጣቱ በመጤ ባህል መወረሩ ሌላው አስቸጋሪ ሁኔታ እንደሆነ ጠቅሰው ለችግሮቹ መባባስ የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ጭምር አስተዋጽኦ አድረገዋል ብለዋል፡፡

ሀገራት ባህሎቻቸውን ከማሳደግ ባሻገር እንዳይበረዙ ህግ አውጥተው እንደሚጠብቁ የተናገሩት አስተያየት ሰጪው በኢትዮጵያ መሰል ህግ እንደሌለ ተናግረዋል፡፡

በዚህም ምክንያት አንድ ሰው እርቃኑን ቢሄድ እንኳን የሚጠይቀው እንደሌለ አመልክተዋል፡፡

አሁን በተከሰተው የባህል ወረራ የተተኪውን ትውልድ ግራ መጋባት ይታይበታል ብለዋል፡፡

ይህን ከማስተካከል ጀምሮ የሀገሪቱን ሠላም በዘላቂነት ለማስቀጠል በሚደረገው ጥረት ሃይማኖታዊ እሴቶችን እና ባህሎችን የመጠበቅ ስራ ልዩ ትኩረት ይፈልጋል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ገጠር አካባቢዎች በስራ አጋጣሚ መዘዋወራቸውን የተናገሩት ሌላው የፌስቲቫሉ  አቶ መሃመድ ኢብራሂም አብሮ መብላትን ጨምሮ የኢትዮጵያውያን የጋራ እሴቶች እየጠፉ መሆኑን እንደታዘቡ አስረድተዋል፡፡

ምክንያቱ ደግሞ ባህሉን በማሳደግ ረገድ በሚፈለገው ልክ አለመስራቱ  እንደሆነ አመልክተዋል፡፡

አሁን ለሚታዩ ያልተለመዱ ግጭቶች ባህላችንን ጠብቀን ለትውልድ አለማስተላለፋችን አስተዋጽኦ አድርጓል ያሉት ደግሞ አቶ ሃሰበላ አዜን ናቸው፡፡

ባህሎቻችንን ጠብቆ በማስተላፍ ረገድ የድርሻችንን መወጣት አለብን ብለዋል፡፡

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ባህል እና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ ወይዘሪት መስኪያ አብደላ ክልሉ የመከባበር ባህል በተቃራኒ ሰዎች የሚሞቱበት እና የሚፈናቀሉበት መሆኑ ቁጭት ያሳድራል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ክልሉ ወደ ቀደመ ሠላሙ ሙሉ በሙሉ እንዲመለስ በጠንካራ ባህላዊ እሴቶችን ላይ በኢትዮጵያዊነት ስሜት በቁጭት ለመስራት መነሳት አለብን ብለዋል፡፡

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ተወካይ አቶ ባበክር ከሊፋ በበኩላቸው  በክልሉ ሠላም መጠናከር ከመንግስት ጥረት በተጨማሪ ቤተሰብ ወሳኝ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ለዚህ ደግሞ ልጆቻቸውን ዘመናዊ ትምህርት ብቻ ሳይሆን ሃይማኖታዊ እሴቶቻቸውን በሚገባ እንዲረዱ ማድረግ እንደሚያስልግ ገልጸዋል፡፡

በክልሉ  ባህሎችን ለማስተዋወቅ የተጀመሩ በጥናት የተደገፉ ተግባራት መኖራቸውን ጠቁመው  ባህልን በማስጠበቅ ረገድ የታዩ ችግሮች እንዲወገዱ ጥረቱ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል፡፡

በፌስቲቫሉ ባህል እና ቋንቋን የሚያስተዋውቅ ጥናታዊ ጽሁፍ፣ባህላዊ ምግብ እና ሙዚቃዎችም  የቀረቡ  ሲሆን አራት መጽሐፍትም  መመረቃቸውን ኢዜአ ከአሶሳ ዘግቧል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም