በመዲናዋ የኮቪድ-19 መከላከያ መመሪያዎችን ለማስተግበር በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ይሰማራሉ

79

ሚያዚያ 2/2013 (ኢዜአ) የአዲስ አበባ ወጣቶችና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ቢሮ የኮቪድ-19 መከላከያ መመሪያዎችን ለማስተግበር በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችን ከፖሊስ አባላት ጋር በማስተባበር እንደሚያሰማራ አስታወቀ።

ቢሮው ኮቪድ-19ን ለመከላከል የወጡ መመሪያዎች እንዲተገበሩ ከጤና ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፣ ከአዲስ አበባ ጤና ቢሮና ፖሊስ ኮሚሽን ጋር በቅንጅት ለመስራት ምክክር አድርጓል።

በኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከል ተግባር ለሚሰማሩ የፖሊስ አባላትና በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችም ዛሬ የስራ ስምሪት ተሰጥቷል፡፡

የቢሮው የበጎ ፈቃድ ዘርፍ ምክትል ሃላፊ አቶ ፍሰሀ ጥበቡ የኮቪድ ወረርሽኝ መስፋፋትን ተከትሎ ለኅብረተሰቡ ግንዛቤ የመፍጠር ሰፊ ስራ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።

ወረርሽኙ የበርካታ ዜጎችን ሕይወት እያሳጣ በመሆኑ ኮቪድን ለመከላከል የወጣውን መመሪያ በአግባቡ መተግበር እንደሚያስፈልግም አስታውሰዋል።

ለዚሁ ሲባል ቢሮው በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችን ከፖሊስ አባላት ጋር በማስተባበር ለማሰማራት ማቀዱንም ነው የገለጹት።

ከመጪው ማክሰኞ ጀምሮም ለአንድ ወር  ሰፊ እንቅስቃሴ ባለባቸው በገበያ፣ በትራንስፖርትና በማምለኪያ ስፍራዎች ኅብረተሰቡ ራሱን እንዲጠብቅ የማስገንዘብ ስራ ይሰራል ብለዋል፡፡

ለዚህም በሁሉም ክፍለ ከተሞች በሚገኙ 60 ፖሊስ ጣቢያዎች በእያንዳንዳቸው 20 በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች መመደባቸውን አስታውቀዋል።

ለአንድ ወር ጊዜም ኅብረተሰቡ የኮቪድ መመሪያዎችን በተገቢው እንዲተገብር የማድረግና የማስገንዘብ ስራ ይሰራል ነው ያሉት፡፡

 
የዚሁ ኮቪድን የመከላከል ተግባር ውጤት ታይቶም በመጪው ምርጫ ኅብረተሰቡ ለኮቪድ ተጋልጭ ሳይሆን ተሳታፊ እንዲሆን የማድረግ ስራ ለመስራት ታቅዷል እንደ አቶ ፍስሀ ገለጻ።

ቢሮው በዚህ ስራ ለሚሰማሩ አካላት የደንብ ልብስ፣ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል፣ ሳኒታይዘርና ሌሎች አስፈላጊ ግብዓቶችን እንደሚሸፍን ገልፀዋል፡፡

በጤና ሚኒስቴር የኮቪድ-19 ግብረ ሃይል ሀላፊ ዶክተር ሊሻን አድማሱ በበኩላቸው አብዛኛው የኅብረተሰብ ክፍል ስለ ኮቪድ መከላከያ መንገዶች ግንዛቤ ቢኖረውም የአተገባበር ክፍተት ይስተዋልበታል ብለዋል።

ኮቪድ-19 ወደ አገሪቷ ሲገባ የወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መነሳት፣ የትምህርት ቤቶች መከፈትና በዓላትና የተለያዩ ዝግጅቶች መከናወን በኅብረተሰቡ ዘንድ የነበረውን ስጋት ወደ መዘናጋት ቀይሮታል ነው ያሉት።

ወረርሽኙ አሁን ካለው በላይ የከፋ ጉዳት ከማስከተሉ በፊት በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችና ሌሎችም የኅብረተሰብ ክፍሎች ኃላፊነታቸውን እንደወጡም ጥሪ አቅርበዋል፡፡ 

የማኅበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አገልግሎት ኃላፊ ኢንስፔክተር ክንዴ መሰረት እየደረሰ ያለውን ጉዳት ለመቀነስ የኮቪድ-19 መከላከል መመሪያዎችን የማይፈፅሙ አካላትን ተጠያቂ የማድረግ ስራ ይሰራል ብለዋል፡፡

ወጣቶች በሽታውን መቋቋም እችላለሁ፣ እከላከለዋለሁ ከሚል የተሳሳተ አመለካከት በመታረም አስፈላውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉም አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም