ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ አስር የድህረ ምረቃ ፕሮግራሞችን ሊከፍት መሆኑን አሰታወቀ

115

ሀዋሳ፣ ሚያዚያ 2/2013 (ኢዜአ) ሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ሁለት የህክምና ስፔሻሊቲን ጨምሮ የተለያዩ አስር የድህረ ምረቃ ፕሮግራሞችን ሊከፍት መሆኑን አስታወቀ።

የዩኒቨርሲቲው ህክምናና ጤና ሣይንስ ኮሌጅ ያስተማራቸውን የህክምና ዶክተሮች ዛሬ በሀዋሳ ዋናው ካምፓስ  አስመርቋል።

የኮሌጁ ኤክስኩዩቲቪ ዳይሬክተር ዶክተር አንተነህ ጋዲሣ በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ እንደገለጹት፤ ኮሌጁ ስራ ከጀመረ ከ1995 ዓ.ም ጀምሮ በህክምና  ዘርፍ   ብቁ ባለሙያዎችን ለማፍራት ጠንክሮ ሲሰራ ቆይቷል።

ዛሬ የተመረቁትን ጨምሮ በ12 ዙር 1ሺህ 551 የህክምና ዶክተሮችን በማስመረቅ ስራ ላይ ማሰማራቱን ጠቅሰዋል።

ከመጀመሪያ ህክምና ዶክተሮች በተጨማሪ በስድስት ስፔሻሊቲ ፕሮግራሞች የዛሬዎቹን 48 ተመራቂዎችን ጨምሮ 129 ስፒሻሊስት ሀኪሞችን ለምረቃ አብቅቷል ብለዋል።

በዚህ ዓመትም በአጥንትና በመንጋጋ ቀዶ ጥገና አዲስ ሰልጣኞችን በመቀበል ማስተማር መጀመሩን አመልክተዋል።

በቅርቡም ሁለት የህክምና ስፔሻሊቲን ጨምሮ የተለያዩ አስር  የድህረ ምረቃ ፕሮግራም ለመክፈት የሥርዓተ ትምህርት ቀረፃ በማጠናቀቅ ላይ መሆኑን አስታውቀዋል።

የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ኢንጅነር ፍሰሀ ጌታቸው በበኩላቸው  ተቋሙ ለምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር  ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ጠቁመው  በበጀት ዓመቱ ብቻ  ከ600 በላይ የምርምር ጽሁፎች (አርቲክል) በታወቁ ጆርናሎች ለህትመት መብቃታቸውን ገልጸዋል።  

ከነዚህም  30 በመቶ የሚሆነው በህክምናና ጤና ሣይንስ ኮሌጅ በሚገኙ ተመራማሪዎች ለህትመት የበቁ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

የምርምርና የቴክኖሎጂ ሽግግርን ተደራሽ ለማድረግ በተለያዩ ወረዳዎች ባቋቋምናቸው የቴክኖሎጂ ሽግግር መንደሮች እየሰራን ነው ብለዋል።

በተለይ ዩኒቨርሲቲው ለሣይንስና ቴክኖሎጂ እንዲሁም ሒሳብ ትምህርት ጥራት መጎልበት ከፍተኛ አስተዋዕኦ የሚያበረክት ማዕከል በማቋቋም በአካባቢው ለሚገኙ የመጀመሪያና ሀለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሚገኝ አውስተዋል።

በክብር እንግድነት በመገኘት በትምህርታቸው ብልጫ ላመጡ ተመራቂዎች ሽልማት ያበረከቱት የሀዋሳ ከተማ ምክትል ከንቲባ ረዳት ፕሮፌሰር ፀጋዬ ቱኬ ናቸው።

በዚህ ወቅት ባደረጉት ንግግር  የእናንተን እርዳታ የሚሹ ወገኖቻችሁን የሙያው ስነ ምግባር በሚያዘው መሰረት ያለምንም የዘር፣ የእምነትና የቀለም ልዩነቶች  የታካሚዎቻችሁን ሚስጢር በመጠበቅ ማገልገል ይጠበቅባችኋል ብለዋል።

ከሰልጣኞቹ መካከል በከፍተኛ ማዕረግ  የተመረቀው ዶክተር ዮናስ ንጉሴ በሰጠው አስተያየት  የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን እየተከላከለ ጠንክሮ በመማር ለውጤት መብቃቱን ገልዖ በተማረበት መስክ ሀገሩንና ህዝቡን፣ በቅንነትና በታማኝነት ለማገልገል መዘጋጀቱን አስረድቷል።

ሌላዋ ተመራቂ ዶክተር ሲፈን ኤፍሬም በበኩሏ፤ የህክምና ሙያ የሚጠይቀውን ከፍተኛ መስዋዕትነት በመክፈል ለምረቃ በመብቃቷ መደሰቷን ገልፃ ህዝቡ የሚፈልገውን አገልግሎት በመስጠት ያሉትን የጤና ችግሮች ለማቃለል በርትታ እንደምትሰራ ተናግሯለች።

ኮሌጁ በአሁኑ ወቅት   2 ሺህ 375 የህክምናና የጤና ሳይንስ ተማሪዎችን እያሰለጠነ  እንደሚገኝ በምርቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም