እናት ፓርቲ በወልድያ ከተማና አካበቢው ማኒፌስቶውን አሰተዋወቀ

69

ወልድያ ሚያዚያ 2/ 2013 (ኢዜአ) እናት ፓርቲ ለምርጫው የመወዳደሪያ ማኒፌስቶውን ዛሬ በወልድያ ከተማና አካበቢው ለአባላቱና ደጋፊዎቹ አስተዋወቀ።

የፓርቲው የወልድያና አካባቢው ሊቀመንበር ዶክተር ደርበው ንጉሤ በወቅቱ እንዳሉት፤ፓርቲው በሃገሪቱ ቋንቋን መሰረት ያደረገው የፌደራሊዝም ስርዓት እንዲስተካከል ይሰራል።

ዜጎች በእኩልነት፣ ልዩነትን በሚያስተናግድ አንድነትና ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በየትኛውም ክልል የመኖርና ሃብት የማፍራት መብቱ እንዲከበር እንደሚሰራ ገልጸዋል።

እናት ፓርቲ "እኛና እነሱ" የሚለው አስተሳሰብ በማስወገድ "እኛ " በሚል አስተሳሰብ እንደሚያራምድም አመልክተዋል፡፡

ፓርቲው አስር  ቁልፍ እሴቶችና መርሆዎች ቀርፆ ለመጪው ምርጫ አማራጭ ሃሳብ ይዞ መቅረቡን ገልጸው ፤የግለሰብ ነፃነትን ቀዳሚ በማድረግ ፍትህ፣ ዴሞክራሲና እኩልነት በሀገሪቱ እንዲሰፍን አበክሮ እንደሚሰራም ተናግረዋል።

ኢትዮጵ በቀጥታ በሕዝብ በሚመረጥ ፕሬዚዳንት የምትመራ ሃገር እንድትሆንም ለምርጫው የመወዳሪያ ሃሳብ ይዞ መቅረቡን ተናግረዋል።

ስድስተኛው ጠቅላላ  ምርጫ ያለምንም ጫና ነፃ፣ ፍትሃዊ፣የሁሉንም ትብብር የሚጠይቅ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህ ምእንዲሳካም እናት ፓርቲ በአባላቱና ደጋዎቹ ግንባር ቀደም ሆነው ይሰራሉ ብለዋል።

የፓርቲው አባል ወጣት አማረ መስፍን በሰጠው አስተያየት ምርጫው ምንም ይሁን ምንም በሰላማዊ መንገድና ዴሞክራሲን ወደ አንድ ደረጃ በሚያሻግር አግባብ እንዲከናወን የድርሻውን እንደሚወጣ ገልጿል።

ብልጽግናና ተፎካካሪ ፓርቲዎች በነፃነት ፕሮግራማቸውን ለህዝብ አቅርበው እንዲወዳደሩ የተጀመሩ ትብብሮችም ተጠናክረው እንዲቀጥሉም መልዕክት አስተላልፏል።

ሌላው የፓርቲው ደጋፊ   ወጣት ንጉሥ ቢልልኝ በበኩሉ ሀገራዊና ዘመናዊ የአመራር እሴት አዋህዶ መጠቀም የሚለው ርእዮተ ዓለም የፓርቲው መልካም እይታ ነው ብሏል።

ምርጫው ሰላማዊ እንዲሆንም መንግስትም ሆነ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በጋራና በሃላፊነት ሊሰሩ እንደሚገባ አስተያየቱን ሰጥቷል።   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም