በደቡብ ወሎ ዞን የሚገኙት የሎጎና አርዲቦ ሐይቆችን ከጥፋት የመታደግ ስራ ተጀመረ

120

ደሴ፤ሚያዚያ 2/2013 (ኢዜአ) የሎጎና አርዲቦ ሐይቆች ከተጋረጠባቸው የመጥፋት አደጋ ለመታደግ የተቀናጀ ስራ መጀመሩን የአማራ ክልል የጣና ሀይቅና ሌሎች የውሃ አካላት ልማትና ጥበቃ ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡

ኤጀንሲው ሃይቆችን ከጥፋት ለመታደግ በሚቻልበት ዙሪያ  ከወሎ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የውይይት መድረክ ዛሬ በደሴ ከተማ ተካሄዷል፡፡

በውይይት መድረኩ የኤጀንሲው ስራ አስኪያጅ ዶክተር አያሌው ወንዴ በክልሉ ያሉ ሀይቆች፤ ወንዞች፤ግድቦችና ውሃ አዘል መሬቶች በሰው ሰራሽና ተፈጥሮ አደጋ ለችግር መጋለጣቸውን ተናግረዋል፡፡

ከእነዚሁ ውስጥም ለጎና አርዲቦ ሀይቆች በልቅ ግጦሽ፣ ደለል፣ ህገ ወጥ አሳ አስጋሪዎች፣ በከተማ  መስፋፋት፣ ቆሻሻና የእርሻ አጠቃቀም ችግር የመጥፋት አደጋ ተደቅኖባቸዋል ብለዋል፡፡

ከችግሩ ተላቀው የገቢ ምንጭ ማስገኛ፤ መዝናኛና የስራ እድል መፍጠሪያ እንዲሆኑ ከወሎ ዩኒቨርሲቲና ባለድርሻ አካላት ጋር ስራ መጀመራቸውን ዶክተር አያሌው ገልጸዋል፡፡

ዘላቂ መፍትሄ ለማበጀት፣ አካባቢው እንዲለማና እንዲጠበቅ በጥናትና ምርምር የታገዘ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመው፤ ለአካባቢው ማህበረሰብ ችግሩን ከማሳየት ባለፈ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ እየተከናወነ መሆኑንም  ጠቅሰዋል።

አርሶ አደሩም ውሃው ሲሸሽ እየተከተለ እንዳያርስና በጎርፍ የሚገባውን ደለል ለመከላከል አካባቢውን በቋሚ አትክልትና ፍራፍሬ እንዲያለሙ ስምምነት ላይ ተደርሶ ችግኝ ተከላ መጀመሩን አሰረድተዋል።

ደሴና ኮምቦልቻ ከተሞችን ከለጎና አርዲቦ ሐይቆች ጋር በማስተሳሰር ለዜጎች የስራ እድል መፍጠርና ሃብት ማመንጨት እንዲችሉም ይሰራል ብለዋል፡፡

የወሎ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ዶክተር አፀደ ተፈራ በበኩላቸው፤ ሐይቆች የተደቀነባቸውን ችግር ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት በዩኒቨርሲቲው የአባይና አዋሽ ተፋሰስ የሚል ተቋም ተቋቁሞ ሐይቆች ላይ ጥናት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በጥናቱ ውጤት ላይ ተመርኩዞ ለማልማትና ለመጠበቅ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይትና ግንዛቤ ፈጠራ ስራ እየተከናወነ ነው ብለዋል፡፡

ሐይቆች ከሚደርስባቸው ጉዳት ለመታደግ የዞኑ፣ አዋሳኝ ወረዳዎችና ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር እየተሰራ መሆኑን የገለፁት ደግሞ የተሁለደሬ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተስፋየ መኩንን ናቸው።

ልቅ ግጦሽ እንዲቆምና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች በዙሪያው እንዲተከሉ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

ህገ ወጥ አሳ አስጋሪዎች በመከላከልና የሎጅ አጠቃቀሙን በማስተካከል የሚደርሰውን ብክለትም ለመከላከል ጥረት እየተደረገ ቢሆንም ጠንካራ ቅንጅት እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል፡፡

በውይይት መድረኩ ከክልል፣ ወሎ ዩኒቨርሲቲ፣ ዞንና ወረዳ የተውጣጡ አመራሮች፣ ባለሙያዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም