ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ከጀመራቸው ችግር ፈቺ የምርምር ፕሮጀክቶች 109 ማጠናቀቁን አስታወቀ

117

ሐረር ፤ ሚያዚያ 1/2013(ኢዜአ) ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰቡን ችግር ለመፍታት ከጀመራቸው የምርምር ፕሮጀክቶች መካከል 109ኙን በማጠናቀቅ ለተጠቃሚው ማመቻቸቱን አስታወቀ።

ዩኒቨርሲቲው የምርምር ስርጸትና ማህበረሰብ አገልግሎት ዓመታዊ ጉባኤውን ከትናንት ጀምሮ እያካሄደ ነው።

በዚህ ወቅት የዩኒቨርሲቲው የምርምር ቡድኖችና አጋርነት ዳይሬክተር ዶክተር ደርባቸው በቃና  በተለይ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ተቋሙ የአካባቢውን አርሶ አደርና የሌላውም ማህበረሰብን ፍላጎት መሰረት በማድረግ ችግር ፈቺ የምርምርና ስርጸት ስራ እያከናወነ ይገኛል።

ባለፉት ሁለት ዓመታት ከጀመሯቸው 229 የምርምር ፕሮጀክቶች መካከል 109 ማጠናቀቃቸውንና ቀሪዎቹ በሂደት ላይ እንዳሉ ገልጸዋል።

ከምርምር ፕሮጀክቶቹ መካከል በ85 የገበሬ ማሰልጠኛ ተቋማት እና ሞዴል የአርሶ አደር ማሳ ምርትና ምርታማነት በሚያሳድጉ በእንስሳት ሀብት ልማት፣ አዝዕርትና ተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራዎች ይገኙበታል።

ከተጠናቁትም ውስጥ 47 የቴክኖሎጂ ፕሮጀክቶች በድሬዳዋ አስተዳደር፣ ምስራቅ እና ምዕራብ ሐረርጌ 16 ወረዳዎች ለሚገኙ ከ62ሺ በላይ አርሶ አደሮች በማሰራጨት ጥቅም ላይ እንዲውሉ ማመቻቸታቸውን ዶክተር ደርባቸው አስታውቀዋል።

የቴክኖሎጂ ፕሮጀክቶቹ በሽታን ተቋቁመው በአጭር ጊዜ ምርት የሚሰጡ እና በዘመናዊ መንገድ የግብርና አሰራርን የሚያቀላጥፉ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ኮሮናን ለመከላከል የሚያግዙ 32 የምርምር ስራዎች ዩኒቨርሲቲው እያከናወነ መሆኑንና ዘንድሮ እንደሚጠናቀቁ  ጠቁመዋል።

ለምርምር ፕሮጀክቶች መንግስት፡ በውጭና ሀገር ውስጥ የልማት ድርጅቶች ከ120 ሚሊየን ብር በላይ የገንዘብ ድጋፍ ማድረጋቸውን የተናገሩት ደግሞ  የዩኒቨርሲቲው የምርምር ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ተስፋዬ ለማ ናቸው።

በተለይ በምርምርም ሆነ በማህበረሰብ አገልግሎት እየተሰሩ የሚገኙት ስራዎች የአርሶ አደሩንና የሌላውም ማህበረሰቡን ችግር የሚፈቱ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በዩኒቨርሲቲው የሚከናወኑ የምርምርና ስርጸት ፕሮጀክቶችን ወደ ቴክኖሎጂ እና ፖሊሲ ግብዓት ከመተግበር አኳያ የሚታዩ ክፍተቶች ለማስተካከል በቀጣይ በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ተወካይ ፕሮፌሰር መንግሰቱ ኡርጌ በበኩላቸው ኮሮና ቫይረስን ከመከላከል አኳያ በችግሩ ዙሪያ ምርምር በማካሄድ በተገኘው ውጤትም ማህበረሰቡን የማንቃትና የመደገፍ ስራ ማከናወናቸወን ገልጸዋል።

በተጨማሪ  ዩኒቨርሲቲው የቆላ ስንዴን በመስኖ ለማምረትና ለማስረጽ የጀመረውን ስራ ለማጎልበት ዝርያን የመለየትና በቴክኖሎጂ የማዳበር ስራ እያከናወነ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።

ዛሬም በቀጠለው የዩኒቨርሲቲው ዓመታዊው የምርምርና ስርጸት ጉባኤ ላይ የልማት ሰራተኞች ፣አርሶ አደሮች፣ ተመራማሪዎች፣መምህራንና ሌሎች መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ መስሪያ ቤት ተወካዮች እየተሳተፉ ነው።

ከጉባኤው በተጓዳኝም በዩኒቨርሲቲው የተሻሻሉ የግብርና ቴክኖሎጂ አውደ ርዕይና ለማህበረሰቡ አገልግሎት የተከናወኑ የድጋፍ ስራዎች እየቀረቡ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም