የቴክኖሎጂና የተግባር ውድድሩ ሀገር አቀፍ ተወዳዳሪነትን ሊያጠናክር በሚችል መልኩ መደገፍ ይኖርበታል -መምህራን

69

አሶሳ ሚያዚያ 1 / 2013 (ኢዜአ) እየወሰድነው ያለው የቴክኖሎጂና ተግባራዊ የጥናትና ምርምር ውድድሩ ሀገር አቀፍ ተወዳዳሪነትን በሚያጠናክር መልኩ ሊደገፍ ይገባል ሲሉ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ መምህራን ጠየቁ።

በክልሉ ሁለተኛው ዙር የክህሎት ቴክኖሎጂና ተግባራዊ የጥናትና ምርምር ውድድር በአሶሳ እየተካሄደ ነው፡፡

በውድድሩ ከተሳተፉ የቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ መምህራን መካከል አሰልጣኝ ቴዎድሮስ ተስፋዬ ለኢዜአ እንደገለጹት በክልል ደረጃ የሚካሄደው ውድድር አሸናፊ በሃገር አቀፉ ውድድር ይሳተፋል፡፡

"እየተሰጠ የሚገኘው የተግባርም ሆነ ሌሎች ፈተናዎች መምህራን መመዘን የማያስችሉ ናቸው" ያሉት መምህር ቴዎድሮስ ውድድሩን እያደረጉ ያለው በወዳደቁ ግብዓቶች እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

በሃገር አቀፍ ደረጃ በሚካሄደው ውድድር ብቁ እንዳንሆን ያደርገናል የሚል ስጋት እንዳሳደረባቸው መምህሩ አስረድተዋል፡፡

የሚመለከተው አካል ለጉዳዩ ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ ጠይቀዋል።

ሌላዋ ተወዳዳሪ አሰልጣኝ ፈንታነሽ ገለታ በበኩላቸው "በውድድሩ ያለንን እውቀት ተጠቅመን ተሳተፍን እንጂ ተጨማሪ የተወዳዳሪነት አቅም አላገኘንም" ብለዋል፡፡

የቁሳቁስ ችግር በስልጠና ወቅት እንደምንም የሚታለፍ ቢሆንም በክህሎት ውድድር ወቅት ግን ተወዳዳሪነትን ሊያሳንሱ ከሚችሉ ጉዳዮች አንዱ ሊሆን እንደሚችል አስረድተዋል፡፡

በክልሉ ፈተና መሰጠት ከተጀመረበት ካለፈው ዓመት አንስቶ የግብዕት እጥረት ጨምሮ ተወዳዳሪነትን የሚቀንሱ ችግሮች እንዲፈቱ በተደጋጋሚ ብንጠይቅም ምላሽ አላገኘን ብለዋል፡፡

በክልሉ ቴክኒክና ሙያ ስራ እድል ፈጠራ ኤጀንሲ የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክተር አቶ ከተማ በቀለ በክልሉ ለሁለተኛ ጊዜ የሚካሄደው ውድድር ዓላማ ዘርፉን ማስተዋወቅ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የቴክኒክና ሙያ ሰልጣኞችና አሰልጣኞች እንዲሁም ኢንተርፕራይዞችን ማነቃቃት የውድድሩ አላማ እንደሆነ ጠቁመው ፈጠራን እንደሚያሻሻል አመልክተዋል፡፡

"ይሁንና ዘርፉ ለሃገር ልማት ከሚሰጠው ጠቀሜታ አንጻር በሚፈለገው ልክ የተደራጀ ነው ማለት አያስደፍርም" ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ሰልጣኞቹ በውድድር ያነሱት ችግር ዋነኛ ምክንያት ዘርፉ ከፍተኛ ካፒታል መጠየቁ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

"ዘርፉ ለሃገር የሚያስፈልገውን መካከለኛ የሰው ሃይል እንዲያሟላ እያደረገ ያለውን አስተዋጽኦ በሚገባ በማስተዋወቅና ሁሉንም ባለድርሻ አካላት በማሳተፍ ለችግሮቹ መፍትሔ በማምጣት ረገድ ጠንካራ ስራ ይጠብቀናል" ብለዋል፡፡

ጅምሩ በመንግስት ብቻ የሚደረገውን ቴክኒክና ሙያ ተቋማትን የማስፋፋትና ማጠናከር ስራ በመደገፍ የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት እንደሚያስችል ጠቁመዋል፡፡

እስከ ሚያዚያ 02  ቀን 2013 ዓ.ም በሚቆየው ውድድሩ መምህራኑ በሚያስተምሩባቸው ዘርፎች በተግባር የተደገፈ ፈተና እንደሚወስዱ ከመርሀ ግብሩ ለማወቅ ተችላል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም