አቶ ደመቀ መኮንን የአፍሪካ ሕብረት ኮምሽን ምክትል ሊቀ-መንበርን ተቀብለው አነጋገሩ

70

አዲስ አበባ ሚያዚያ 01 ቀን 2013 (ኢዜአ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በቅርቡ የአፍሪካ ሕብረት ኮምሽን ምክትል ሊቀ-መንበር ሆነው የተመረጡት ዶ/ር ሞኒክ ንሳንዛባጋንዋን ዛሬ በጽህፈትቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

አቶ ደመቀ የአፍሪካ ሕብረት ኮምሽኑ ምክትል ሊ/መንበር ሆነው በመመረጣቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው፤ በቀጣይ በሚኖራቸው የስራ እንቅስቃሴ አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግላቸው አረጋግጠውላቸዋል።

በመቀጠልም አቶ ደመቀ በቅርቡ በኪንሻሳ የተካሄደው የታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ድርድርን በተመለከተ ያብራሩላቸው ሲሆን አፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ ማገኘት እንዳለባቸው በማመን በአፍሪካ ሕብረት አስተባበሪነት የሚካሄደው የሶስትዮሽ ድርድር እንዲቀጥል በኢትዮጵያ በኩል ጽኑ እምነት ያለ መሆኑን ገልጸውላቸዋል።

በትግራይ ክልል ያለው የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት በመሻሻል ላይ መሆኑን ለምክትል ሊቀ-መንበሯ አብራርተውላቸዋል።

ዶ/ር ሞኒክ ንሳንዛባጋንዋን በበኩላቸው ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ መርህ በአፍሪካ ሕብረቱ በኩል በጽኑ የሚታመን መርህ መሆኑን ገልጸው፣ ኢትዮጵያ በዚህ አንጻር ለያዘችው አቋም ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል።

በሌላ በኩል በአሁኑ ወቅት ያጋጠመውን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ለመከላከል በሚደረገው ጥረት የሕብረቱ ሰራተኞች ክትባት አንዲደርሳቸው በኢትዮጵያ መንግስት በኩል ድጋፍ አንዲደረግ ጥያቄ አቅርበዋል።

አቶ ደመቀ ለአፍሪካ ሕብረት ሰራተኞች ተገቢው የክትባት አገልግሎት እንዲደርሳቸው ማደረጉ ተገቢ መሆኑ ገልጸው፣ ለተፈጻሚነቱም ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በትብብር እንደሚሰራ ገልጸውላቸዋል።

በመጨረሻም አቶ ደመቀ መኮንን ለዶ/ር ሞኒክ ንሳንዛባጋንዋን መልካም የስራ ዘመን አንዲሆንላቸው ተመኝተው፣ ለስራቸው ስኬትም በኢትዮጵያ በኩል አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግላቸው አረጋግጠውላቸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም