በኢትዮጵያ በአይነቱ የመጀመሪያ የሆነ የምልክት ቋንቋ ማስተርጎሚያ ሶፍትዌር ይፋ ሆነ

125

መጋቢት 30/2013(ኢዜአ) በኢትዮጵያ በአይነቱ የመጀመሪያ የሆነው የምልክት ቋንቋ ማስተርጎሚያ ሶፍትዌር ይፋ ተደርጓል።

የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኝነትና ልማት ማዕከል ከአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ጋር በጋራ ያዘጋጁትን የምልክት ቋንቋ ማስተርጎሚያ ሶፍትዌር ይፋ አድርገዋል።

ሶፍትዌሩ በዋናነት መስማት የተሳናቸው ሰዎች ከሀኪሞች ጋር ያለ ሶስተኛ ወገን ወይም አስተርጓሚ በቀላሉ ለመግባባት የሚያስችላቸው ነው ተብሏል።

ይህም ምስጢራቸው ተጠብቆ ሕክምና ለማግኘት ያግዛቸዋል ነው የተባለው።

ማስተርጎሚያ ሶፍትዌሩ የምልክት ቋንቋን ወደ ድምጽ እና ጽሁፍ መልዕክት በመለወጥ በሀኪሙና በመስማት የተሳነው ታካሚ መካከል መግባባት እንደሚፈጥር ተመላክቷል።

ይህንን ሶፍትዌር አበልጽጎ ስራ ለማስጀመር ሁለት ዓመታት መፍጀቱም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኝነትና ልማት ማዕከል የፋይናንስ አስተዳደር ሃላፊ አቶ ከበደ ከድር እንዳሉት አካል ጉዳተኞች በጤና ተቋማት የተለያዩ ችግሮች ያጋጥሟቸዋል።

ከችግሮቹ መካከል መስማት ለተሳናቸው ዜጎች በጤና ተቋማት አስተርጓሚ አለመኖር ምክንያት ከጤና ባለሙያዎች ጋር ለመግባባት ሲቸገሩ ይታያል ብለዋል።

በተለይም የስነ ተዋልዶና የኤች.አይ.ቪ ኤድስ ህክምና አገልግሎቶች ምስጢራዊነታቸው ስለማይጠበቅ በሶስተኛ ወገን እጅ በመውደቁ ችግር ሲፈጥር እንደሚታይ ጠቁመዋል።

በመሆኑም ማዕከሉ ከፓካርድ ፋውንዴሽን ባገኘው ድጋፍ ከአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የምልክት ቋንቋ ማስተርጎሚያ ሶፍትዌር ማበልፀጋቸውን ገልጸዋል።

ይህም መስማት የተሳናቸው ዜጎች በጤና ተቋማት ውስጥ ያለማንም አስተርጓሚ ምስጢራቸው ተጠብቆ አገልግሎት እንዲያገኙ ይረዳቸዋል ብለዋል።

የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር አብርሃም ደበበ በበኩላቸው ተቋሙ የቴክኖሎጂና የልህቀት ማዕከል እንዲሆን መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ጋር እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ይፋ የሆነው ሶፍትዌር ለዚህ ማሳያ እንደሆነ ገልጸው በቀጣይ ወደስራ ከገባ በኋላም እንደ አስፈላጊነቱ ማሻሻያዎች እንደሚደረጉበት አስረድተዋል።

ዩኒቨርሲቲው አገራዊ ጠቀሜታ ያላቸው፣ የኅብረተሰቡን ኑሮ የሚቀይሩ፣ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳቸው የጎላና በቴክኖሎጂ የተደገፉ ምርምሮችን በመደገፍ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል።

የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ ዮናስ ተስፋዬ በበኩላቸው በርካታ የስነ-ተዋልዶና ተያያዥ ጥያቄዎች በስፋት በሶፍትዌሩ ውስጥ መካተታቸውን ገልጸዋል።

የምልክት ቃላት ውስብስብና ከቦታ ቦታ የተለያዩ በመሆናቸው በተቻለ አቅም ያማክላሉ የተባሉ ከ16 ሺህ በላይ የምልክት ቃላት እንደተካተቱበትም ጠቁመዋል።

መስማት የተሳነው ሰው በምልክት በሚያወራበት ወቅት የሚያደርጋቸውን እንቅስቃሴዎች ለዚህ ተብሎ በተዘጋጀ መሳሪያ በመመዝገብ በሶፍትዌሩ አማካኝነት ምልክቶቹን ወደ ድምጽ እና ጽሁፍ እንደሚቀይርም አስረድተዋል።

ቴክኖሎጂው በተለያዩ ጊዜያት ማሻሻያ ቢፈልግ የሚደረግበት በመሆኑ በቀጣይ ለሚሰሩ መሰል ስራዎች ፈር ቀዳጅ መሆኑን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም