ኢትዮጵያ በአፍሪካ ወጣቶች ኦሎምፒክ ውድድር ላስመዘገበችው ዝቅተኛ ውጤት ኃላፊነቱን እወስዳለሁ-የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ

68
አዲስ አበባ ሀምሌ 23/2010 ኢትዮጵያ በአፍሪካ ወጣቶች ኦሎምፒክ ውድድር ላይ ላስመዘገበችው ዝቅተኛ ውጤት የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ኃላፊነቱን እንደሚወስድ  አስታወቀ። የኦሎምፒክ ኮሚቴ የስራ ኃላፊዎች በአልጄሪያ ርዕሰ መዲና አልጀርስ በተካሄደው 3ኛው የአፍሪካ ወጣቶች ኦሎምፒክ ኢትዮጵያ ያስመዘገበችውን ውጤትና የአፍሪካ ኦሎምፒክ ኮሚቴዎች ማህበር (አኖካ) በአልጀርስ ስላካሄደው አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ ዙሪያ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል። የአፍሪካ ወጣቶች ኦሎምፒክ ከሐምሌ 11 እስከ 21 ቀን 2010 ዓ.ም የተካሄደ ሲሆን ኢትዮጵያ በ11 ወርቅ፣ ስምንት የብርና ስድስት የነሐስ ሜዳሊያ በድምሩ 25 ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ ሰባተኛን ደረጃ ይዛ ማጠናቀቋ የሚታወስ ነው። አትሌቲክስ፣ ወርልድ ቴኳንዶ፣ ብስክሌትና ቦክስ ኢትዮጵያ ሜዳሊያ ያገኘችባቸው የስፖርት አይነቶች ናቸው። አትሌቲክስ፣ ቦክስ፣ ወርልድ ቴኳንዶ፣ ካራቴ፣ ብስክሌትና ጠረጴዛ ቴኒስ ኢትዮጵያ በውድድሩ ላይ የተሳተፈችባቸው የስፖርት አይነቶች ናቸው። የኢትዮጵያ አሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት ከተደረገው ዝግጅት አንጻር ኢትዮጵያ ያገኘችው ውጤት መልካም የሚባል ነው። በውድድሩ 56 ስፖርተኞችን ያሳተፈው የኢትዮጵያ ልዑክ ለኦሎምፒኩ ዝግጅት ይረዳው ዘንድ ከሁለት እስከ ሶስት ወር ዝግጅት እንዳደረገ ገልጸው ከውድድሩ ባህሪይ አንጻር የተደረገው ዝግጅት በቂ አልነበረም ብለዋል። ከዚህ በተሻለ ለውድድሩ በቂ ዝግጅት ማድረግ ይቻል እንደነበረና ይህም የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ችግርና ክፍተት እንደሆነ ተናግረዋል። በቂ ዝግጅት ያልተደረገበት ምክንያት ኦሎምፒክ ኮሚቴው ተወዳዳሪዎችን የሚመርጥበት የውስጥ ውድድር አለመኖሩና እንደ ሌሎች አገራት የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ የክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት አለመኖሩ እንደሆነ ነው ዶክተር አሸብር ያስረዱት። ይህም በመሆኑ ምክንያት ኮሚቴው በብሔራዊ ስፖርት ፌዴሬሽኖች ላይ ጥገኛ እንዲሆን እንዳደረገውና ይህም ዋጋ እንዳስከፈለው ገልጸዋል። ኦሎምፒክ ኮሚቴው ተወዳዳሪዎችን የሚመርጥበት የውስጥ ውድድር ለማዘጋጀትና የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ የክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች መክፈት የሚያስችል አቅጣጫ እንዳስቀመጠና ለዚህም የሚረዳ ሰነድ እየተዘጋጀ መሆኑን አመልክተዋል። በውድድሩ ላይ ሜዳሊያ የተገኘባቸው ስፖርቶች በመንግስት ብዙ ድጋፍ የማይደርግላቸው እንደሆነ የተናገሩት ዶክተር አሸብር ይህም ኦሎምፒክ ኮሚቴው በጉዳዩ ላይ ቆም ብሎ እንዲያስብ እንደሚያደርገው አስረድተዋል። በውድድሩ ላይ የተሳተፉ ተወዳዳሪዎችና አሰልጣኞች ሳይበተኑ ተጨማሪ ስፖርተኞች በመጨመር በኢትዮጵያ ወጣቶችና ስፖርት አካዳሚ ስልጠና ተሰጥቷቸው በቀጣይ ውድድሮች ላይ ጠንካራ ተፎካካሪ ለመሆን እቅድ መያዙን አብራርተዋል። በቀጣይም በሚካሄዱ የአፍሪካ ወጣቶች ኦሎምፒክ ውድድሮች ላይ ኢትዮጵያ የምትሳተፍበትን የስፖርትና ሜዳሊያ ቁጥር ለማሳደግ እንደሚሰራም ጠቁመዋል። የአፍሪካ ኦሎምፒክ ኮሚቴዎች ማህበር (አኖካ) በአልጀርስ ስላካሄደው አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ አፍሪካ በኦሎምፒክ ውድድር ላይ ያላትን ውጤታማነት ማሳደግ፣በቀጣይ በጃፓን በሚካሄደው የማህበሩ ፕሬዚዳንት ምርጫና አስተዳዳራዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ እንደሆነም አክለዋል። የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ዋና ጸሐፊ አቶ ታምራት በቀለ በበኩላቸው በአልጀርሱ ውድድር የወርቅ ሜዳሊያ ያመጡ ኢትዮጵያውያን ስፖርተኞች በቀጣዩ ዓመት በአርጀንቲና በሚካሄደው የዓለም የወጣቶች ኦሎምፒክ ላይ እንደሚሳተፉ ጠቁመዋል። በአትሌቲክስ ውድድር ብርና ነሐስ ሜዳሊያ ያመጡ አትሌቶች አፍሪካ በአርጀንቲናው ውድድር ላይ የሚሰጣት ኮታ ታይቶ በውድድሩ ላይ ሊሳተፉበት የሚችል እድል እንዳለም ጠቅሰዋል። ግብጽ በአልጄሪያ በተካሄደው የአፍሪካ ወጣቶች ኦሎምፒክ በ86 የወርቅ፣ 45 የብርና 32 የነሐስ በድምሩ 162 ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ አንደኛ ሆናለች።   የአፍሪካ ኦሎምፒክ ኮሚቴዎች ማህበር (አኖካ) ሐምሌ 10 ቀን 2010 ዓ.ም በአልጄሪያ ባደረገው አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ ሌሴቶ ከአራት ዓመት በኋላ የሚካሄደውን አራተኛው የአፍሪካ ወጣቶች ኦሎምፒክ እንድታዘጋጅ መወሰኑ የሚታወስ ነው።   ከአራት ዓመት በፊት ሁለተኛው የአፍሪካ ወጣቶች ኦሎምፒክ በቦትስዋና ርዕሰ-መዲና ጋቦሮኒ ሲካሄድ ኢትዮጵያ 14 የወርቅ፣ ስድስት የብር እና ሰባት የነሐስ ሜዳሊያ በማግኘት አምስተኛ ደረጃን ይዛ ማጠናቀቋ አይዘነጋም።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም