የአገር ሠላምና የልማት ጉዳይ የሕዝቦች የጋራ ጉዳይ መሆኑን መገንዘብ ይገባል

70

ሀዋሳ መጋቢት 30/2013 (ኢዜአ) የአገር ሠላም፣ እድገትና የልማት ጉዳይ የሕዝቦች የጋራ ጉዳይ መሆኑን መገንዘብ እንደሚገባ ተነገረ።

የባሕልና ቱሪዝም ሚኒስቴር "የኢትዮጵያዊያን የጋራ ጉዳዮች" በሚል መሪ ሃሳብ በአገሪቷ ታሪክና የጋራ እሴቶች ዙሪያ ከተለያዩ ተቋማት ከተውጣጡ አካላትና ከምሁራን ጋር ተወያይቷል።

የሚኒስትሯ አማካሪ አቶ ወርቅነህ አክሊሉ በአንድ አገር የሚኖሩ ሕዝቦች የኖረ የጋራ ታሪክ እንጂ የተነጣጠለ ታሪክ የላቸውም ሲሉ በውይይቱ ላይ ገልፀዋል።

ኢትዮጵያዊያን ብዝሃነትን የሚሸከም የጋራ ታሪክና እሴት ያላቸው ሕዝቦች እንደመሆናቸው አንድነታቸውን በሚያጠናክሩ ጉዳዮች በሕብረት መቆም ይገባቸዋልም ብለዋል።

በተለይም የአገር ሠላም፣ እድገትና ልማት ጉዳዮች የጋራ መሆናቸውን መረዳት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የስነ-ሰብ እና የማኅበራዊ ሳይንስ ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት ዶክተር አወቀ አምባዬ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያዊያን አንድ የሚያደርግ ታሪክ አላቸው ይላሉ።

በባህል፣ በታሪክ፣ በቋንቋ፣ በማኅበራዊ መስተጋብሮችና በአኗኗር ስርዓት እርስ በርስ የተጋመዱና አንድ የሚያደርጉ እሴቶችን የተላበሱ መሆናቸውን አብራርተዋል።

ልጆች ከህጻንነት ዕድሜያቸው ጀምሮ በኢትዮጵያዊነት ብዝሃነትን በመቀበል የሚያምኑ ሆነው ተኮትኩተው እንዲያድጉ ከታች ጀምሮ መሰራት አለበት ነው ያሉት።   

ለዚህም የጋራ እሴቶችን በመጠበቅ የሕዝቦች አንድነት እንዲጠናከር ትውልዱ ስለ ታሪኩና ባሕሉ አጥብቆ እንዲረዳ ማስተማር ይገባል ብለዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ኢትዮጵያዊያን አንድ የሚያደርጓቸው የጋራ እሴቶች እየተሸረሸሩ ስለመምጣታቸው አንስተዋል።

በዚህም ለአገር ቅድሚያ በመስጠት የሚያጋጥሙ እንከኖችን በመለየት በሠላም ግንባታና በጋራ መግባባት ላይ አንድነትን በማጠናከር አሁን የገጠሙ የሰላም እጦት ችግሮችን በጋራ መግታት ይገባል ብለዋል።

ሠላምና ዴሞክራሲ ለማስፈን ከተለያዩ አቅጣጫዎች የሚሰነዘሩ አጥፊ ሃሳቦችን ወደጎን በመተው ችግሮችን ለመፍታት የሚያግዙ ማኅበራዊ ሃብቶችን ማዳበር እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል።

በትምህርት የተገነባና አገሩን፣ ታሪኩንና ባሕሉን የሚወድ ትውልድ ማፍራት ከተቻለ የጋራ እሴቶችን መጠበቅ እንደሚቻል አብራርተዋል።

ለዚህም የአገር መሪዎች፣ ልሂቃን፣ የማኅብረሰብ አንቂዎችና በማኅበረሰቡ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው ሰዎች የችግሮች መንስኤ ሳይሆን የሠላም ሰባኪዎች ሊሆኑ ይገባቸዋል ብለዋል የውይይቱ ተሳታፊዎች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም