በጋምቤላ ከተማ ሁለገብ የህፃናትና የወጣቶች የስዕብና መገንቢያ ማዕከል ሊገነባ ነው

100

ጋምቤላ፤ መጋቢት 30/2013(ኢዜአ) በጋምቤላ ከተማ 11 ሺህ 557 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ሁለገብ የህፃናትና የወጣቶች የስዕብና መገንቢያ ማዕከል ሊገነባ መሆኑ ተገለጸ።

የጋምቤላ ከልል ርዕሰ መስተዳድር  አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በተገኙበት ለማዕከሉ ግንባታ በተዘጋጀው ዲዛይን ዙሪያ በጋምቤላ ከተማ ውይይት ተካሄዷል።

በውይይት መድረኩ እንደተገለጸው፤ ማዕከሉ "ገበታ ለጋምቤላ" ሚል በህዝብ ተሳትፎ  ከ35 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገነባ ነው።

በጋምቤላ ከተማ በባሮ ወንዝ ዳርቻ "ጂኒና" ስፍራ የሚገነባው ይኸው ሁለገብ የህፃናትና የወጣቶች የስዕብና መገንቢያ ማዕከል ከ17 በላይ የአገልግሎት መስጫዎችን ያካትታል።

በማዕከሉ ከተካቱት የአገልግሎት መስጫዎች ውስጥ ቤተ መፃፍት፣ የመረጃ ማዕከል፣ የጤና ስነ-ተዋልዶ፣ የቦሊቦል፣ ቅርጫት ኳስ ሜዳዎችና፣ የመዋኛ ገንዳ ይገኙበታል።

"ገበታ ለጋምቤላ" ማዕከል ግንባታ አንድ ዓመት ባልፈጀ ጊዜ ሊጠናቀቅ እንደሚገባ በውይይት መድረኩ የተሳተፉ አመራሮች ተናግረዋል።

ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በመድረኩ እንዳሉት፤ ካሁን በፊት በክልሉ ለህፃናትና ወጣቶች ምቹ የእርፍት ጊዜ ማሳለፊያና መማሪያ ቦታ በበቂ ሁኔታ ባለመኖሩ አለባሌ ቦታ በመዋል ለተለያዩ ማህበራዊ ችግሮች ሲዳረጉ ቆይተዋል።

በመልካም ስብጽናና አእምሮ የተገነባ የነገ ሀገር ተረካቢ ዜጋ ለማፈራት ትውልዱ በእርፍት ጊዜው የሚዝናናበትና እውቀት የሚገበይበት ምቹ ቦታ መፍጠር ይገባል ብለዋል።

የማዕከሉ ግንባታ እውን በማድረግ ወጣቱን ከችግር ለመታደግ ሁሉም የክልሉ ህዝብ ሁለንተናዊ ተሳትፎ ተጠናከሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አሳስበዋል።

እንደ ሀገር በተጀመሩት የገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች የክልሉ ህዝብ ያሳየውን ተሳትፎ ገበታ ለጋምቤላ ሁለገብ የህፃናትና የወጣቶች ስብዕና ማዕከልም ግንባታ ላይ  መድገም  እንዳለበትም አመልክተዋል።

ለማዕከሉ ግንባታ እውን መሆን ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረከትም ርዕሰ መስተዳድሩ ጥሪ አቅርበዋል።

ገበታ ለሀገር ፕሮጀክት ክልሉ ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉን አውስተዋል።

የሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ አለሚቱ ኡሞድ በበኩላቸው ወጣቶች በእረፍት ጊዜያቸው ከአልባሌ ቦታ እንዲርቁ   ምቹ ቦታ እንደሚያስፈልጋቸው ተናግረዋል።

አሁን ላይ መንግስት የወጣቱን የመዝናኛና የእረፍት ጊዜ ማሳለፊያ ጥያቄ ምላሽ በመስጠት ለአጓጉል ሱስናና ሌሎች ችግሮች ተጋላጭነትን ለመቀነስ በገጠርና በከተማ የስብና መገንቢያ ማዕከል ልማትን እያካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።

በጋምቤላ ክልል የወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በመንግስት ለተጀመረው ጥረት ስኬታማነት ህዝቡ ተሳተፎውን ሊጠናከር እንደሚገባ አሳስበዋል

ሚኒስቴሩ ለማዕከሉ ግንባታ እውን መሆን የተጀመረው ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ሚኒስትር ዴኤታዋ  አስታውቀዋል።

የጋምቤላ ክልል ሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ ሀላፊ ወይዘሮ አጁሉ አቻር የማዕከሉ የግንባታ ዲዛይን በማዘጋጀት ረገድ የሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ሚኒስቴር ላደረገው ድጋፍ ምስጋና  አቅርበዋል።

በቀጣይም የማዕከሉ ግንባታ እውን እስኪሆን የሚኒስቴሩ  ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም