ኢትዮ-ቴሌኮም በምስራቅ ምስራቅ ሪጅን የ4G ኢንተርኔት አገልግሎት አስጀመረ

81

መጋቢት 30/2013 (ኢዜአ) ኢትዮ-ቴሌኮም በምስራቅ ምስራቅ ሪጅን የ4G ኤል.ቲ.ኢ አድቫንስድ ኢንተርኔት አገልግሎት በይፋ አስጀምሯል።

የሶማሌ ክልል ሰባት ከተሞችን ተጠቃሚ ያደርጋል የተባለው የ'4G ኤል.ቲ.ኢ አድቫንስድ አገልግሎት በጂግጂጋ ከተማ ነው ለምረቃ የበቃው።

አገልግሎቱ ጂግጂጋ፣ ጎዴ፣ ቀብሪ ደሃር፣ ቀብሪ በያህ፣ ደገሃቡር፣ ፊቅና ዋርዴር ከተሞች የሚገኙ 454 ሺህ ደንበኞችን ተጠቃሚ ለማድረግ ያለመ መሆኑ ተገልጿል።

የኢትዮ-ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ወይዘሪት ፍሬህይወት ታምሩ እንደገለጹት የማስፋፊያ አገልግሎቱ በአንድ ወር ውስጥ ተደራሽ ተደርጓል።

የ4G ኢንተርኔት አገልግሎት ደንበኞች ዘመኑን የሚመጥን ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኙ ያደርጋል ብለዋል።

በተጨማሪም አገልግሎቱ በአካባቢው ለሚገኙ ደንበኞች ጥራት ያለውና አስተማማኝ አገልግሎት ማግኘት ያስችላል ነው ያሉት።

በመሆኑም ኢትዮ-ቴሌኮም አስቸጋሪ መልክዓ ምድር ባለበት አካባቢ አገልግሎቱን ለምስራቅ ምስራቅ ሪጅን ተደራሽ በማድረጉ ደስተኛ ነው ብለዋል ዋና ስራ አስፈጻሚዋ።

የ'4G ኢንተርኔት ምስሎችን በፍጥነት ለመጫንና ለማውረድ፣ የቀጥታ ፕሮግራሞችን ሳይቆራረጡ በኢንተርኔት ለመከታተል ምቹ እንደሆነም ነው ያስረዱት።

በተፋጠነና በተቀላጠፈ መልኩ ግብይት ለማካሄድና የልማት ስራዎችን ለማስኬድም እስካሁን ካሉት የኢንተርኔት አማራጮች የተሻለ መሆኑን አብራርተዋል።

ዋና ስራ አስፈጻሚዋ እንዳሉት ኢትዮ-ቴሌኮም የሶስት ዓመት ስትራቴጂ በመቅረፅ በርካታ የአገልግሎት ማሻሻያ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል።

እስካሁን አገልግሎቱ ባልተዳረሰበት አካባቢ ማድረስ፣ የአገልግሎት ጥራት የማሻሻልና የማሳደግ ስራዎችን ጠቅሰዋል።

ዘመኑ የሚፈጥራቸውን አዳዲስ አገልግሎቶች ለደንበኞች ተደራሽ ማድረግም በዕቅድ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮ-ቴሌኮም የቴሌኮም መሰረተ ልማቶችን በማስፋፋት የአገሪቱን የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ እንደሚያግዝም ነው ዋና ስራ አስፈጻሚዋ የተናገሩት።

በኢትዮጵያ 25 ሚሊዮን የሚጠጉ የሞባይል ኢንተርኔት ተጠቃሚዎች የሚገኙ ሲሆን ከዓለም ሕዝብም 52 በመቶ ሰዎች የ4G ኢንተርኔት አገልግሎት ተጠቃሚ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም