ኢትዮጵያና ሩሲያ በጉምሩክ ዘርፍ ያደረጉት ስምምነት ማፅደቂያ ረቂቅ አዋጅ ለውጭ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተላለፈ

73
አዲስ አበባ ግንቦት 7/2010 የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በኢትዮጵያና በሩሲያ በጉምሩክ ዘርፍ የተደረገው ስምምነት ማፅደቂያ ረቂቅ አዋጅ በዝርዝር እንዲታይ ለውጭ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አስተላለፈ። ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው 3ኛ ዓመት የስራ ዘመን 24ኛ መደበኛ ጉባኤው በስምምነቱ ላይ ተወያይቶ በዝርዝር እንዲታይ ለውጭ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቷል። ስምምነቱ የኢትዮጵያና ሩሲያ የጉምሩክ ዘርፍ ትብብርና አስተዳደራዊ ድጋፍ የሚያትት  ሲሆን፤ የካቲት 21 ቀን 2005 ዓ.ም ነበር በሁለቱ አገራት ተወካዮች የተፈረመው። ሩሲያ በንግድና በኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎቿ ጠንካራ ከሚባሉ አገሮች ተርታ የምትመደብ በመሆኗ ኢትዮጵያ የጉምሩክ ህጎችና ስነ-ስርዓቶችን ማስከበርና በቴክኖሎጂ ሽግግር ከፍተኛ ልምድ ታገኝበታለች ተብሏል። በስምምነቱ የጉምሩክ ጥፋቶችን በመከላከል፣ በመመርመርና በመግታት ረገድም በትብብር እንደሚሰሩ ተገልጿል። የጉምሩክ ቀረጥ አሰባሰብ እና የግብይት ዋጋና የስሪት  አገርን የማረጋገጥ ስራዎችንም በጋራ እንደሚሰሩ ስምምነቱ ያትታል። የጉምሩክ ስነ ስርዓቶችን የተመለከቱ ምርምሮችን በጋራ የመስራትና የባለሙያዎች ስልጠናን ጨምሮ የጋራ ጥረትን የሚጠይቁ ስራዎች ላይ በትብብር እንደሚሰሩም ተገልጿል። በዓለማችን ማህበረሰባዊ ደህንነትን አደጋ ላይ የሚጥለውን የአደገኛ እፅ ዝውውር ለመከላከልና ለመግታትም በጋራ የሚያሰራ ስምምነት ነው ተብሏል። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስምምነቱን ለማፅደቅ መዘግየቱን ያነሱት የምክር ቤቱ አባላት፤ በስሩ ያሉት ድንጋጌዎች በቋሚ ኮሚቴዎቹ በጥልቀት እንዲታዩም አሳስበዋል። ስምምነቱ እስካሁን የዘገየበት ምክንያት ግን አልተገለፀም። ስምምነቱ እንዲጸድቅ በሚያስችለው ደረጃ በዝርዝር እንዲታይና በዋናነት ለውጭ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ በተባባሪነት ደግሞ ለገቢዎችና ጉምሩክ ቋሚ ኮሚቴ ተመርቷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም