ለወራት ከአገልግሎት ውጪ ሆኖ የቆየው የተከዜ የውሃ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ዛሬ ሥራ ጀመረ

86

መጋቢት 29 ቀን 2013 (ኢዜአ) ለወራት ከአገልግሎት ውጪ ሆኖ የቆየው የተከዜ የውሃ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ዛሬ ሥራ መጀመሩን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ።

የኃይል ማመንጫ ጣቢያው ከብሔራዊ የኃይል ቋት (ግሪድ) ጋር የሚገናኝበት መስመር በመቋረጡ ምክንያት ኃይል ማመንጨት አቁሞ እንደነበር ይታወሳል።

ከተከዜ- መቀሌ በተዘረጋው የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ላይ ሲደረግ የነበረው ጥገና በመጠናቀቁ ዛሬ ከቀኑ 7 ሰዓት ጀምሮ በጊዜያዊነት ከሲስተም ጋር ሳይገናኝ ራሱን በራሱ እየተቆጣጠረ (Isolated mode) ኃይል መስጠት ጀምሯል።

በአሁኑ ሰዓት ጣቢያው ካሉት አራት ዩኒቶች መካከል በሁለት ዩኒቶች እስከ 108 ሜጋ ዋት ድረስ ኃይል እየሰጠ ይገኛል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ካለፈው ሐሙስ ከሰዓት ጀምሮ በትግራይ ተቋርጦ የነበረው የኤሌክትሪክ አገልግሎት ዛሬ ከተከዜ ኃይል ማመንጫወደ መቀሌ የሚሄደው መስመር ተጠግኖየተከዜ ኃይል ማመንጫ ስራ በመጀመሩ ዳግም አገልግሎት ማግኘት መጀመሩ ታውቋል።

ቀደም ሲል ከአላማጣ መኾኒ አሸጎዳ መቀሌ የሚሄደው መስመር ላይ ባጋጠመ ችግር ምክንያት የትግራይ ክልል ኤሌክትሪክ ተቋርጦ ነበር።

በትግራይ የተካሄደውን የህግ ማስከበር ተከትሎ በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ላይ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰ ሲሆን የተከዜ ግድብ ደግሞ መንግስት በአውሮፕላን ደብድቦ አፍርሶታል ተብሎ የሀሰት ወሬ ተናፍሶ እንደነበርም ይታወሳል።

በወቅቱም በግድቡ ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት እንዳልደረሰ መገለጹም እንዲሁ።

የተከዜ የውሃ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ በአራት ዩኒቶች 300 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም እንዲኖረው ተደርጎ የተገነባ ባለ ጥምር ቅስት (double arc)ቅርፅ የኃይል ማመንጫ ጣቢያ መሆኑ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም