መከላከያ ሰራዊት"በትግራይ ክልል ንጹሃንን ፈጅቷል"በሚል በጁንታው ተላላኪዎች የሚናፈሰው የተቀነባበረ የሃሰት ወሬ ነው ... መከላከያ ሚኒስቴር

196

አዲስ መጋቢት 29/2013(ኢዜአ) መከላከያ ሰራዊት " በትግራይ ክልል ንጹሃንን ፈጅቷል " በሚል በጁንታው ተላላኪዎች የሚናፈሰው የተቀነባበረ የሃሰት ወሬ መሆኑን የሀገር መከላከያ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ይህንኑ የፈጠራ ወሬ በሚመለከት በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች የተለቀቀው ቪዲዮም በጁንታው ተላላኪዎች በውሸት ተቀናብሮ ህዝብ ለማደናገር የተሰራ መሆኑ ተገልጿል።

የመከላከያ ኢንዶክትሪኔሽን ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጀነራል መሀመድ ተሰማ ወቅታዊ ጉዳዮችን አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

በመግለጫቸውም የመከላከያ ሰራዊቱ ባካሄደው የህግ ማስከበር ዘመቻ ጽንፈኛውን የህወሓት ቡድን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መደመሰሱን ገልጸዋል፡፡

ይሁን እንጂ አሁንም አንዳንድ የጁንታው ርዝራዦች የሸፍታነትን ባህሪ ለመላበስ በጫካ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ መኖራቸውን ጠቅሰዋል።

በዚህም በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች በአሳቻ ስፍራ ላይ እየተገኙ በህዝቡ ላይ ዘረፋ፣ እንግልትና ግዲያ እየፈፀሙ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የጁንታው ርዝራዦች ሰላማዊ ሰዎችን በመጨፍጨፍ አገርና ህዝብን እየጠበቀ ባለው የሀገር መከላከያ ሰራዊት የተፈፀመ ለማስመሰል እየጣሩ መሆኑን አብራርተዋል።

የፅንፈኛ ቡድኑ ተላላኪዎች በጁንታው ታጣቂ ሃይል የተፈፀመውን ግዲያ የምስል ቅንብር በመስራት የሀገር መከላከያ ሰራዊት የፈፀመው አስመስለው ማሰራጨታቸውን ሜጀር ጀነራል መሀመድ አስታውስዋል።

የሀገር መከላከያ ሰራዊት በከፍተኛ ስነ ምግባር የተገነባ ህዝባዊ መሰረት ያለው የህዝብ ልጅ በመሆኑ ህዝብን የሚጎዳ ተግባር አይፈፅምም ነው ያሉት።

የህወሃት ጁንታ ዘራፊ ቡድን ጫካ ውስጥ ሆኖ የተሳሳቱ ትርክቶችን በማስተላለፍ በህይወት እንዳለ ለማስመሰል ልዩ ልዩ ተግባራትን በማከናወን ላይ ይገኛልም ነው ያሉት።

በውጭ ሃይሎች ተቀባይነትን አግኝተናል እያሉ በማደናገር ወጣቶችን ለእኩይ አላማቸው ለማሰለፍ ያደረጉት ጥረትም አለመሳካቱን አብራርተዋል።

በተለያዩ ቦታዎች መሽጎ የሚንቀሳቀሰው ቀሪ የጁንታው ቡድን የሎጀስቲክ እና ሌሎች መሰረታዊ አቅርቦቶች ስለሌላቸው ህዝቡን በማስፈራራትና በመዝረፍ ህይወታቸውን ለማቆየት እየጣሩ መሆኑንም ሜጀር ጀነራል መሀመድ ተናግረዋል።

በአሁኑ ጊዜም ቀሪ የጁንታው ርዝራዥ በትግራይ ክልል የህዝብ ተቀባይነት ስለሌለው በዜጎች ላይ የዘረፋና ግዲያ ወንጀሉን ቀጥሏል ብለዋል።

በክልሉ ቀሪ የጁንታውን ርዝራዦች ለማደን በሚደረገው ጥረት ህዝቡ እስካሁን ለሰራዊቱ ያደረገውን ድጋፍ ያደነቁት ሜጀር ጀነራል መሀመድ በቀጣይም እንዲጠናከር ጠይቀዋል።

መከላከያ ሰራዊት ቀሪ ርዝራዦችን በማደን ይዞ ለህግ ለማቅረብ ሌት ተቀን እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም