በኢትዮጵያ ዘመናዊ ቴአትር የተጀመረበት 100ኛ ዓመት ከቀጣዩ ወር ጀምሮ ይከበራል

144

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 29/2013 (ኢዜአ)  በኢትዮጵያ ዘመናዊ ቴአትር የተጀመረበት 100ኛ ዓመት ከቀጣዩ ወር መግቢያ ጀምሮ “ቴአትርን ማነቃቃት” በሚል መሪ ሀሳብ እንደሚከበር የኢትዮጵያ ቴአትር ባለሙያዎች ማኅበር ገለፀ።

የማኅበሩ ፕሬዚዳንት ደራሲና ዳይሬክተር ቢኒያም ወርቁ በሰጠው መግለጫ በዓሉ ከሚያዝያ 5 ቀን 2013  ጀምሮ ቴአትር ወደነበረበት ከፍታ ለመመለስና ለማነቃቃት በሚያስችሉ ዝግጅቶች እንደሚከበር አስታውቋል።

በዝግጅቱ የፈጠራ ሥራዎች ያላቸውን ባለሙያዎች ከተመልካቾች ጋር ለማገናኘትና ከመንግሥትና መንግሥታዊ ካልሆኑ አካላት ጋር መወያየትን ታሳቢ አድርጓል ብሏል።

በበዓሉ ታላላቅ የቴአትር ባለሙያዎች፣ ዩኒቨርሲቲዎች፣ የቴአትር ትምህርት ቤቶችና መገናኛ ብዙኃንን ያሳተፉ ዝግጅቶች እንደሚቀርቡ አመልክቷል።

በተጨማሪም ቴአትሮች፣ ሙዚቃ፣ ቴአትር ቤቶችና የውጭ አገራት ባህል ማዕከላት በቴአትር የነበራቸውን ድርሻ የሚያሳይ ዐውደ ርዕይ እንደሚካሄድና ምክክር እንደሚደረግ አስታውቋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቴአትር ጥበባት ትምህርት ቤት መምህር ረዳት ፕሮፌሰር ዘሪሁን ብርሃኑ በዓሉ የተቀዛቀዘውን የቴአትር እንቅስቃሴ በሚያነቃቃ መልኩ ይከበራል ብለዋል።

በተለይም በአገሪቱ በነበሩ አስተዳደራዊ ፣ ኢኮኖሚያዊ ፣ፖለቲካዊ ችግሮች የተዳከመውን ቴአትር እንዲያሰራራ ትኩረት መሰጠቱን ገልጸዋል።

በአገር አቀፍ ደረጃ 100 ቴአትሮች የሚቀርቡባቸው ፌስቲቫሎች እንደሚዘጋጁም አስታውቀዋል።

ለዘርፉ አንጋፋ ባለሙያዎች የዕውቅና እና የምስጋና ሥነ ሥርዓት ይካሄዳልም ብለዋል። 

ደራሲና ዳይሬክተር መዓዛ ወርቁ በበኩሏ በዓሉ ሰዎች ቴአትር ለማዘጋጀትና ለመፃፍ እንዲበረታቱ ታስቦ መዘጋጀቱን ትናገራለች። 

ለበዓሉ መክፈቻ  “የካሣ ፈረሶች” እና “ሼክስፒር ኢትዮጵያዊ ነው” በሚል ርዕሶች የተዘጋጁ አዳዲስ ቴአትሮች እንደሚቀርቡ አስታውቃለች።

"የአውሬዎች መሳለቂያ ኮሜዲ" /ፋቡላ/ የተሰኘው የመጀመሪያው አውሮፓዊ ቅርፅ ያለው ቴአትር በበጅሮንድ ተክለሐዋርያት ተክለማርያም ተዘጋጅቶ ከቀረበ ዘንድሮ አንድ ምዕተ ዓመት ሞልቶታል።

የዓለም የቲአትር ታሪክ በ6ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጥንታዊ ግሪኮች አስገራሚና አዝናኝ ድራማዊ አቀራረቦችን በማዘጋጀትና በማቅረብ እንደጀመሩት ይነገራል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም