ይስማ ንጉስ ሙዝየምን ለጎብኝዎች ክፍት ለማድረግ በቅርስ የማደራጀት ስራ ተጀምሯል-መምሪያው

96

ደሴ ፣ መጋቢት 29/2013 (ኢዜአ) በደቡብ ወሎ ዞን አምባሰል ወረዳ በ25 ሚሊዮን ብር የተገነባውን "ይስማ ንጉስ" ሙዝየምን ለጎብኝዎች ክፍት ለማድረግ በቅርስ የማደራጀት ስራ መጀመሩን የዞኑ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ አስታወቀ፡፡

የመምሪያው ኃላፊ አቶ ሱለይማን እሸቱ ለኢዜአ እንደገለጹት "ይስማ ንጉስ" የአደዋ ጦርነት መነሻ፤ ኢትዮጵያና ኢጣሊያ የውጫሌ ውል ስምምነት የተፈራረሙበት ታሪካዊ ቦታ ነው፡፡

ይሁን እንጅ እስካሁን ሳይለማ በመቆየቱ ታሪኩ ለትውልድ እንዳይተላለፍ ሆኗል በሚል የአካባቢው ህብረተሰብ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ሲያነሳ መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡

የህዝብን ጥያቄ ተከትሎ በስፍራው ላይ የአደዋን ድል፣ የኢትዮጵያን ታሪክና የህብረተሰቡን አንድነት በሚገልጽ መልኩ በ25 ሚሊዮን ብር ወጭ ሙዝየም ተገንብቶ በጥር 2013 ዓ.ም መመረቁን አስታውሰዋል፡፡

ሙዚየሙ መገንባቱ ብቻ በቂ ባለመሆኑ የቱሪስት መዳረሻ ሆኖ እንዲያገለግል ታሪኩን የሚገልፁ ቅርሶችን በማሰባሰብ ከየካቲት 2013 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ሙዚየሙ የማስገባትና የማደራጀት  ስራ መጀመሩን ተናግረዋል።

ከወረዳ እስከ ፌደራል ቅርስ አሰባሳቢ ኮሚቴ ተቋቁሞ ባደረገው ጥረት የኢትዮጵያንና የአደዋን ድል ታሪክ የሚገልጹ ከ1 ሺህ በላይ መጽህፍት ወደ ሙዝየሙ እንዲገቡ መደረጉን ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያና ኢጣሊያ የተፈራረሙባቸው 20 አንቀፆችም በአማርኛና በኢጣሊኛ ቋንቋ በሸክላ ተቀርጸው በሙዚየሙ ውስጥ እንዲቀመጡ መደረጉን አስታውቀዋል።

ተጨማሪ ቅርሶችና ለጦርነቱ ያገለግሉ ጎራዴዎች፣ ጦሮች፣ ጋሻዎችና የተለያዩ አልባሳትን በውርስ፣ በግዥና በስጦታ ለማሰባሰብ ኮሚቴው በቅንጅት እየሰራ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

በአምባሰል ወረዳ ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች ቡድን ባለሙያ ወይዘሮ የውብዳር ሽበሽ በበኩላቸው ሙዚየሙ ጥቁርና ነጮች እኩል መሆናቸውን በሚያሳይ መልኩ የተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የቱሪስት መዳረሻ እንዲሆን መሰረተ ልማቶች እየተሟሉ መሆኑን ጠቁመው "በአደዋ ጦርነት ጥቅም ላይ ውለው የነበሩ ቅርሶች አዲስ አበባ ሙዚየምን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች በመኖራቸው ወደ ስፍራው እንዲመጡ እየተሰራ ይገኛል" ብለዋል።

ትውልዱ ታሪኩን በትክክል እንዲረዳ ለጉብኝት የሚያበቁ ቅርሶች በዚህ ዓመት ተሰብስበው ሙዚየሙን ለጎብኝዎች ክፍት ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

"ሙዚየሙ ቁሳቁስ ተሟልቶለት ለጉብኝት ክፍት እንዲሆን አስፈላጊው ድጋፍ ይደረጋል" ያሉት ደግሞ የወሎ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ዶክተር አፀደ ተፈራ ናቸው።

ሙዚየሙ ለብሔራዊ መግባባትና ሰላም የጎላ ሚና ያለው በመሆኑ ቅርስ በማፈላለግና በገንዘብ በመደገፍ ዩኒቨርሲቲው ኃላፊነቱን እንደሚወጣ አስታውቀዋል።

ሙዚየሙ የጥገናና ምርምር ማዕከል ጭምር እንዲሆን በጥናት የታገዘ ስራ እንደሚከናወን ተጠባባቂ ፕሬዝዳንቱ አስታውቀዋል።

"ስፍራው መላውን የኢትዮጵያ ህዝብ የሚያስተሳስር ታሪካዊ ቦታ ነው " ያሉት ደግሞ የአካባቢው ነዋሪ አቶ ጉግሳ ኡስማን ናቸው።

ለሙዚየሙ አስፈላጊው ቅርስ ተሟልቶለት ለጉብኝት ክፍት እንዲሆን የተጀመረው ስራ የህዝቡን የረዥም ጊዜ ጥያቄ የመለሰ መሆኑን ተናግረዋል ።

"ሙዚየሙ ለአካባቢው ልማትና ለወጣቱ የስራ እድል መፍጠሪያ ከፍተኛ አስተዋዕፆ ስላለው እንክብካቤና ጥበቃ ለማድረግ ዝግጁ ነን" ብለዋል፡፡

ለአደዋ ጦርነት መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ክተት የተጠራበት ታሪካዊ ቦታ በሆነው ወረኢሉ ከተማ ላይም ተመሳሳይ ሙዚየም ለመገንባት እየተሰራ መሆኑን ከመምሪያው የተገኘ መረጃ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም