በኢትዮጵያ ውስጥ የሚከሰቱ ግጭቶችን በተሳሳተ መንገድ መተረክ የሀገሪቱን ህልውና ይፈታተናል ... የፖለቲካና ኢኮኖሚ ተንታኝ ላውረንስ ፍሪማን

88

መጋቢት 29/2013( ኢዜአ) በኢትዮጵያ ውስጥ የሚከሰቱ ግጭቶችን በተሳሳተ መንገድ መተረክ የሀገሪቱን ህልውና የሚፈታተን ነው ሲሉ ታዋቂው የፖለቲካና ኢኮኖሚ ተንታኝ ላውረንስ ፍሪማን ተናገሩ።

የአፍሪካ ጉዳዮች የፖለቲካል ኢኮኖሚ ተንታኝ ላውረንስ ፍሪማን ኢትዮጵያ የወደፊት እጣ ፈንታ ሊያስተካክል የሚችል ሀገር አቀፍ ምርጫ ለማካሄድ በዝግጅት ላይ መሆኗን ጠቁመው በትግራይ ክልል ስለተካሄደው ህግ ማስከበር ዘመቻን በተመለከተ የሚሰጡ የሐሰት ትረካዎች አሁንም ድረስ የተዛቡና አሳሳች መሆናቸውን ገልጸዋል።

በትግራይ ክልል ያለውን ሁኔታ በተመለከተ የተሰሩ አብዛኛዎቹ ዘገባዎች በፌዴራል መንግስት እና በህወሓት መካከል የተፈጠረ አለመግባባት አስመስለው የተቀረጹ የሐሰት ትርክቶች ናቸው በማለት አብራርተዋል።

አንዳንድ ዘገባዎች በሁለት ተቃራኒ የታጠቁ ሃይሎች የተካሄደ ውጊያ አስመስለው የዘገቡ መሆናቸውን ያመለከቱት ተንታኙ፤ ሌሎች ዘገባዎች ደግሞ ህወሃት ክልሉን “ከውጭ ጠላት” ለመከላከል ሲል የወሰደው እርምጃ አስመስሎ በማቅረብ ህጋዊ ለማድረግ መሞከራቸውን ጠቁመዋል።

የህወሃት ቡድን በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት መሰንዘሩን ተከትሎ መንግስት የሀገሪቱን ሉአላዊነት ለማረጋገጥ ወታደራዊ የአጸፋ ምላሽ ለመስጠት መገደዱን ተናግረዋል።

ይህንን ጉዳይ እንዲያጣሩ በፕሬዚደንት ጆ ባይደን ትዕዛዝ ወደ ኢትዮጵያ የተላኩት ልዩ መልዕክተኛ ሴናተር ኩንስ ይዘው የተመለሱት ምላሽ ቀደም ሲል ሲነሳ ከነበረው የተሳሳተ ክስ በተቃራኒው የሚያሳይ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

ኢትዮጵያ በመጪው ግንቦት ወር መጨረሻ የምታካሂደው ሀገር አቀፍ ምርጫ በዓይነቱ የተለየና ታሪካዊ ይሆናል የሚል ዕምነት እንዳላቸውም ጠቁመዋል።

ምርጫው ከብሔር ተኮር ግጭቶች ነጻ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በሀላፊነት መንፈስ እንዲሰራም ተንታኙ ምክራቸውን ለግሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም