ኢትዮጵያ በጤፍ ባለቤትነት ላይ ያጣችውን መብት ለማስከበር ክስ ልትመሰርት ነው

57
አዲስ አበባ ግንቦት 7/2010 ኢትዮጵያ በጤፍ ባለቤትነት ላይ ያጣችውን መብት ለማስከበር ክስ ልትመሰርት መሆኑን የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታወቀ። ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጅነር ጌታሁን መኩሪያ እንዳሉት፤ አገሪቱ ባለፉት ዓመታት የባለቤትነት መብቷን ለማስመለስ ያካሄደችው ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ውጤት አልባ በመሆኑ ክስ የመመስረተ ሂደቱን እንደ አማራጭ ይዛለች። የኔዘርላንዱ ካምፓኒ በጤፍ ዱቄት አዘገጃጀት በአምስት የአውሮፓ አገሮች የባለቤትነት መብት በማግኘቱ ሚኒስቴሩ ለዚህ ጉዳይ ፍትህ ለማግኘት ጥረት እያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል። ጥንቃቄ ባልተሞላበት አካሄድ ከ12 ዓመት በፊት ወደ ኔዘርላንድ የተላከው 10 ያህል የጤፍ ዝርያ ኢትዮጵያ የባለቤትነት መብቷን እንድታጣ ያደረገ መሆኑን አስታውሰዋል። ይህንን የባለቤትነት መብት ለማስመለስ የተጀመረው የዲፕሎማሲ ጥረት ሶስት አመታትን ያስቆጠረ መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትሩ ከዚህ ጎን ለጎን  የፍርድ ሂደቱን ለመጀመር የሚያስችሉ ሰነዶችና ጥያቄዎች ለጠቅላይ ዐቃቤ ህግ  ቀርቧል ብለዋል። ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በቅድሚያ የአገሪቱ ብቸኛ የሆኑ የግብርና ምርቶች በአገር ውስጥ እውቅና በመስጠት ባለቤትነታቸውን በአለም ዓቀፍ ደረጃ ለማስጠበቅ የሚያስችል ስራ በአዕምሯዊ ጽህፈት ቤት በኩል መጀመሩን ገልጸዋል። በተለይ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ችግሮቹን ለመፍታት ከፈረንሳይ ድርጅት ጋር በመተባበር እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል። በተለያየ መንገድ የኢትዮጵያ ብርቅዬ የግብርና ምርቶች ወደ ውጭ ሲላኩ ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበት ሚኒስትሩ አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም