የሴፍቲኔት ተጠቃሚዎች የምግብ ዋስትናቸውን እንዲያረጋግጡ አስፈጻሚው በትኩረት ሊሰራ ይገባል-ቢሮው

151

መጋቢት 29/2013 (ኢዜአ) የ5ኛው ዙር የልማታዊ ሴፍቲኔት መረሃ-ግብር ተጠቃሚዎች የምግብ ዋስትናቸውን በዘላቂነት እንዲያረጋግጡና ሃብት ማፍራት እንዲችሉ አስፈጻሚ አካላት ትኩረት ሰጥተው መስራት እንዳለባቸው የአማራ ክልል ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ አስገነዘበ።

5ኛው ዙር የአማራ ክልል የልማት ሴፍቲኔት መረሃ-ግብር ትላንት በባህር ዳር ከተማ ይፋ ተደርጓል።

በምክትል ርእሰ መስተዳደር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ሙሉነሽ አበበ በመርሃ ግብሩ ማስጀመሪያ ላይ እንደገለጹት በየደረጃው የሚገኙ አስፈጻሚዎችና ባለሙያዎች ማህበረሰቡን ለመለወጥ ሳይታክቱ መስራት ይገባል።

አስፈጻሚ ተቋማትና ባለሙያዎች በልማት ሴፍቲኔት መረሃ-ግብሩ የታቀፉ የህብረተሰብ ክፍሎች ከከፋ ድህነት ተላቀው የራሳቸውን ጥሪት እንዲያፈሩ ማህበረሰባዊ ሃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣትና በቅንጅት ተናቦ መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።

"በህብረተሰባችን ላይ የተጫነውን ድህነት ማስወገድ የሚቻለው ያለ አቅምን አሟጦ መስራት ሲቻል በመሆኑ  ከቸልተኝነትና ምን አገባኝነት በመላቀቅ በቁርጠኝነት ለውጤት መስራት ይገባል" ብለዋል።

ድህነት የእድል ጉዳይ ሳይሆን የስንፍና መገለጫ መሆኑን አመልክተው 5ኛው ዙር የሴፍትኔት መርሀ ግብር የተቀመጠለትን ግብ እንዲመታ የክልሉ መንግስት ተገቢውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።

''የምግብ ዋስትና ችግር የአንድ ዘርፍ ስራ ብቻ አይደለም'' ያሉት ደግሞ የግብርና ሚኒስትር የምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ዳይሬክተር ወይዘሮ ስንታየሁ ደምሴ ናቸው።

ከዚህ ቀደም የነበሩ የአሰራር ክፍተቶችን በመቅረፍ የህብረተሰቡን ኑሮ ለማሻሻል በቅንጅት መስራት ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ተናግረዋል።

በ5ኛው ዙር የልማታዊ ሴፍቲኔት መረሃ-ግብር እንደ ሃገር ከረጂ ድርጅቶችና ከመንግስት የሚገኝ 2 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ ገልጸው በመርሀ ግብሩ 8 ሚሊዮን የሚጠጉ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚሰራ አስታውቀዋል።።

"ከዚህ ቀደም በልማታዊ ሴፍቲኔት መረሃ-ግብር ስራዎች ላይ የነበሩ የብድር አቅርቦት፣ የአቅም ግንባታ ችግሮችና ሌሎችንም በማስተካካል የተለየ ግልጸኝነትና ተጠያቂነት ያለው አሰራር ይተገበራል" ብለዋል።

ለዚህ ደግሞ አስፈጻሚና ባለድርሻ አካላት ለህብረተሰባቸው የኑሮ መሸሻልና መለወጥ ሲሉ በቅንጅትና በትብብር የሚሰሩት ስራ ወሳኝነት እንደሆነ አብራርተዋል።

በአማራ ክልል ለ5 አመት በሚቆየው 5ኛው ዙር የልማታዊ  ሴፍቲኔት መረሃ-ግብር 1 ነጥብ  9 ሚሊዮን በድህነት ላይ ያሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ የገለጹት ደግሞ የአማራ ክልል የአደጋ መከላከል፣ ምግብ ዋስትና ፕሮግራሞችና ልዩ ድጋፍ የሚሹ አካባቢዎች ማስተባበሪያ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘላለም ልጅዓለም ናቸው።

በዚህ ዓመት ከዚህ ቀደም በመርሀ ግበሩ  ታቅፈው የነበሩ 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ተጠቃሚዎችን ይዞ በመቀጠል በቀጣይ ዓመት አዳዲስ ተጠቃሚዎችን የመመልመል ስራ እንደሚከነናወን አስገንዝበዋል።

በልማታዊ ሰፍቲኔት መረሃ-ግብር የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ትኩረት ከሚሰጣቸው ስራዎች መካከል አንዱ እንደሆነ የገለጹት ደግሞ የክልሉ ግብርና ቢሮ ሃላፊ ዶክተር መለስ መኮንን ናቸው።

በተለይም በክልሉ የሚስተዋለውን ከፍተኛ የአፈር መሸርሸር ለመከላከል የመርሀግበሩ ተጠቃሚዎች በስፋት እንደሚሳተፉ አስታውቀዋል።

"በልማታዊ ሴፍቲኔት መረሃ-ግብር አማካኝነት የሚሰሩ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃዎች አካባቢዎችን ካላስፈላጊ ንክኪ በመጠበቅ የውሃ ሃብትን በማበልፀግ ለአካባቢው ነዋሪ ህዝብና ለእንስሳት መጠጥ የጎላ ድርሻ ይኖራቸዋል" ብለዋል።

በኢትዮጵያ የልማታዊ ሴፍቲኔት መረሃ-ግብር ላለፉት 15 አመታት እየተተገበረ ያለመሆኑ ይታወቃል።

በክልል ደረጃ ትላንት በተካሄደው የመርሀ ግበሩ ማስጀመሪያ ስነ ስርአት ላይ የፌደራል፣ የክልሉና የዞን አመራሮች እንዲሁም ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም