በጌዴኦ ዞን የፍትህ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚነሱ ቅሬታዎችን በጥናት ለይቶ ለመመለስ እየተሰራ ነው

114

ዲላ፤ መጋቢት 28/2013 (ኢዜአ) በፍትህ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ህብረተሰቡ የሚያነሳቸውን ቅሬታዎች በጥናት ለይቶ ምላሽ ለመስጠት እየተሰራ መሆኑን የጌዴኦ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ገለጸ።

በፍርድ ቤቶች የሚስተዋለውን የፍትህ መዘግየትና መፍትሄው  ዙሪያ   ዛሬ በዲላ ከተማ የምክክር መድረክ ተካሄዷል።

የዞኑ  ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ሳሙኤል በፍቃዱ በወቅቱ እንዳሉት፤  በየደረጃው የሚገኙ ፍርድ ቤቶች የሚሰጡትን አገልግሎት የተቀላጠፈ ለማድረግ እየተሰራ ነው።

በተለይ ተቋማቱን ስነ ምግባር ባላቸውና  በተማረ የሰው ኃይል፣ ግብአት ለማጠናከር  ጥረት መደረጉን  ጠቅሰዋል።

ሆኖም  ለአዳዲስ መዋቅሮች ምቹ የችሎት ስፍራዎች አለመዘጋጀት፣ ነባሮቹ የአደረጃጀት ችግሮች፣ በፖሊስ፣ አቃቤ ሕግና ጠበቆች አማካይነት በሚፈጠር የምርመራ መዘግየት በዞኑ ለሚስተዋለው የፍትህ መጓደል ተጠቃሽ ምክንያቶች መሆናቸውን በጥናት መለየቱን ጠቁመዋል።

በጥናት የተለዩትን ጨምሮ ሕብረተሰቡ በፍትህ አገልግሎት ላይ ጥያቄ እንዲያነሳ የሚያደርጉ ክፍተቶችን ለማስተካከል ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ባለፉት ስድስት ወራት ውሳኔ ካገኙ 3 ሺህ 18 የክስ መዝገቦች ውስጥ 80 በመቶ ከሁለት ወር በታች በሆነ ጊዜ ውስጥ እልባት መሰጠቱን  አስረድተዋል።

እንደ አቶ ሳሙኤል ገለጻ፤ ተዘዋዋሪ ችሎቶችን፣ የመደበኛ የክስ መዝገብ እንዲሁም ነፃ የህግ አገልግሎት ድጋፍና ሌሎች የፍርድ ቤት አገልግሎቶችን በቴክኖሎጂ በማስደገፉ ረገድ የተከናወኑ ተግባራት ተስፋ ሰጪ መሻሻሎች እየታየባቸው ነው።

ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል አቶ ዝናቡ አበበ በሰጡት አስተያየት፤ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በየደረጃው በሚገኙ በፍርድ ቤቶች አስቸኳይ ውሳኔ ከመስጠት አንጻር የሚስተዋሉ መሻሻሎች የሚበረታቱ  ናቸው ብለዋል።

የፍትህ አካላት ሙያዊ ሥነ ምግባርን በመላበስ ሕዝብና መንግስት የጣለባቸውን ኃላፊነት በቅንነትና በታማኝነት ከመወጣት አንጻር ክፍተት መኖሩን አንስተዋል።

በፍትህ ተቋማቱ መካከል ተናቦ አለመስራት ጉዳዮች እንዲንዛዙ ምክንያት በመሆናቸው ቅንጅታዊ አሰረርን በማጠናከር የህብረተሰቡን የፍትህ ተጠቃሚነት ለማሳደግ ትኩረት እንዲሰጡ  አመልክተዋል።

በፍርድ ቤቶች የተቀላጠፈ ፍትህ በመስጠቱ ረገድ መሻሻሎች ቢኖሩም የሚፈለገው ደረጃ ላይ ደርሷል ለማለት አያስደፈርም ያሉት ደግሞ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሽፈራው ቦጋለ ናቸው።

የዞኑን ሕዝብ የፍትህ ጥማት ለማርካት ፖሊስ ፣አቃቤ ህግና ፍርድ ቤቶች ከእርስ በእርስ ክስ ወጥተው ለተቀላጠፈ ፍትህ ተቀናጅተው ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በዞኑ እየተበራከተ የመጣውን ህገ ወጥ የመሬት ወረራ፣  የሴቶችና ሕፃናት ጥቃት ጉዳይ የተለየ ትኩረት በመስጠት ህጉ የሚፈቅደውን ወሳኔ ለመስጠት አበክረው እንዲሰሩም አመልክተዋል።

የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ለተቀላጠፈ ፍትህ አሰጣጥ ተግዳሮት የሆኑ ጉዳዮችንና መፍትሄዎቻቸው ላይ ጥናት ማካሄዱ በዞኑ ቀልጣፋ የፍትህ ሥርዓት እንዲኖርና የተለዩ ችግሮች እንዲፈቱ  የዞኑ አስተዳደር ለመደገፍ ዝግኩ መሆኑን  አስታውቀዋል።

በምክክር መድረኩ  በየደረጃ የሚገኙ የፍትህ ተቋማት አመራሮችና ባለሙያዎች እንዲሁም ሌሎች  የመንግስት ስራ አስፈጻሚዎችና የህብረተሰቡ ተወካዮች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም