የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ውድድር በታሪኩ በርካታ ድንቅ አትሌሎችን ያፈራ መድረክ ነው- አትሌት ደራርቱ ቱሉ

88

አዲስ አበባ መጋቢት 2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ውድድር በታሪኩ በርካታ ድንቅ አትሌሎችን ያፈራ የውድድር መድረክ መሆኑን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ፕሬዚዳንት ኮማንደር አትሌት ደራርቱ ቱሉ ገለፀች። 50ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ውድድር በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል ።
በመከፍቻው በተለያዩ ርቀቶች ማጣሪያ የተደረገ ሲሆን በጦር ውርወራና በ10 ሺህ ሜትር ሩጫ ማምሻውን የፍፃሜ ውድድር ይካሄዳል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ፕሬዚዳንት ኮማንደር አትሌት ደራርቱ ቱሉ የመክፈቻ ንግግር አድርጋለች።

በ50 ዓመት የሻምፒዎናው ታሪክ አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ፣ ጌጤ ዋሜ፣ ገዛኸኝ አበራና ሌሎችም ድንቅ አትሌቶች የተገኙበት መሆኑን አስታውሳ የአሁኑም ውድድር በኦሊምፒክና በዓለም ሻምፒዎና ሀገርን የሚወክሉ አትሌቶች የሚወጡበት ነው ብላለች።

በአልጄሪያ አልጀርስ ለሚካሄደው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና እና በቶኪዮ ኦሊምፒክ የሚሳተፉ አትሌቶችን ለመምረጥ ያገዛል ነው ያለችው።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ1963 ዓ.ም የተጀመረ ሲሆን በዘንድሮ ሻምፒዮና 507 ሴቶችና 736 ወንድ አትሌቶች ተሳታፊ ይሆናሉ ተብሎ ያጠበቃል። 

ባለፈው ዓመት 49ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና በኮቪድ-19 ምክንያት ሳይካሄድ የቀረ ሲሆን በ48ኛው ሻምፒዮና በሴቶች መከላከያ በወንዶች ኦሮሚያ ክልል በአጠቃላይ ደግሞ መከላከያ ማሸነፉ የሚታወስ ነው።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና የ50ኛው የወርቅ ኢዮቤልዩ ውድድር ከዛሬ ጀምሮ እስከ ሚያዚያ 3 ቀን 2013 ዓ.ም በተለያዩ ውድድሮች ይካሄዳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም