በሰሜን ሸዋ ዞን 100 ሺህ ሄክታር መሬት ያካለለ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ መከናወኑ ተነገረ

166

ፍቼ መጋቢት 28/2013/ኢዜኣ/-በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በህዝብ ተሳትፎ 100 ሺህ ሄክታር መሬት ያካለለ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ መከናወኑን የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ፅህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራዎቹ ገቢያቸውን ለመጨመርና የግብርና ስራቸውን ውጤታማ ለማድረግ እየረዷቸው መሆኑን አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ  የዞኑ አርሶ አደሮች ተናግረዋል፡፡

የፅህፈት ቤቱ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ  ቡድን መሪ አቶ ግርማ አሰፋ ለኢዜአ እንደገለፁት በዞኑ በዘንድሮ በጋ በ13 ወረዳዎች 350 ሺህ ህዝብ በማሳተፍ 100 ሄክታር መሬት ያካለለ የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራ ተከናውኗል።

ከተከናወኑት የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች መካከል ከ2ዐ ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ የእርከንና 1ሺህ 3ዐዐ ኪሎ ሜትር የጐርፍ መቀልበሻ ቦይ እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።

 የጐርፍ ውሃን በማቆር የአፈር እርጥበትን ለመጠበቅ የሚያግዙ ከ260 ሺህ በላይ ትናንሽ የውሃ ጉድጓዶች  መቆፈራቸውን አመልክተዋል።

በጐርፍ ተጐድቶ የቆየ ከ6ዐ ሺህ ሄክታር በላይ መሬት የማካለል ስራ መከናወኑንም ተናግረዋል ።

እንደ ቡድን መሪው ገለጻ በህዝቡ ነጻ ጉልበት የተከናወነው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ  ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ ይገመታል

ከተሳታፊ አርሶ አደሮች መካከል የግራር ጃርሶ ወረዳ የቶርባን አሼ ቀበሌ ነዋሪ ጫላ በየነ የአፈርና ወሀ ጥበቃ ስራ የአፈር ለምነትን በመጠበቅ ለግብርና ምርታማነት መሰረት የሚጥል ወጤት እያመጣ መሆኑን

ተናግረዋል ።

ዘንድሮ  ለ4ዐ ቀን በተካሄደ የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራ የነቃ ተሳትፎ ማድረጋቸውን ገልጸዋል ።

"የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ ለሁለገብ የግብርና ስራ ውጤታማነት አስፈላጊ መሆኑን በማመን በልማት ቡድን ተደራጅተን የሚጠበቅብንን አበርክተናል" ያሉት ደግሞ በወረዳው የወርጡ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አየለ ባንቲሁን ናቸው።

በየአመቱ እየተካሄደ ባለው የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራ የአካባቢያቸውን የቀድሞ ለምነት ለመመለስ ፣የደረቁ ምንጮች እንዲያገግሙና በተለይም ለንብ ማነብ ስራ ከፍተኛ አስተዋጻ ማድረጉን አርሶ አደር አየለ አስታውቀዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም