ኢስት አፍሪካን ቦትሊንግ ኩባንያ በልደታ ክፍለ ከተማ ለነዋሪዎች ያስገነባቸውን ሱቆች አስረከበ

116

አዲስ አበባ መጋቢት 2013 (ኢዜአ) ኢስት አፍሪካን ቦትሊንግ ኩባንያ በአዲስ አበባ ልደታ ክፍለ ከተማ ያስገነባቸውን ሱቆችና የህዝብ መፀዳጃ ቤት ለወጣቶች አስረከበ ፡፡

ኩባንያው በአዲስ አበባ ከተማ ልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሶስት ያስገነባቸውን 8 ሱቆችና አንድ የህዝብ መፀዳጃ ቤት ነው በዛሬው እለት ያስረከበው።

የኩባንያው የዘላቂነት ልማት ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ሙሴ ግርማ፤ ኩባንያው ማህበራዊ ሃላፊነቱን ለመወጣትና ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ ከ1 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ ግንባታ ማከናወኑን ገልጸዋል።

ኩባንያው ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት የጀመረውን ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።

የልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሶስት ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ እንግዳው ጓዴ በበኩላቸው ለወጣቶች የስራ እድል በመፍጠር ረገድ ውስንነቶች እንዲኖር ካደረጉ ጉዳዮች መካከል የመስሪያ ቦታ እጥረት ዋነኛው መሆኑን ተናግረዋል።

ችግሩን በመንግስት አቅም ብቻ መቅረፍ አዳጋች በመሆኑ የሌሎች ባለድርሻ አካላት ድጋፍ ያስፈልጋል ነው ያሉት።

በመሆኑም የወረዳ አስተዳደሩ በወረዳው ካሉ በጎ አድራጊ ማህበራት፤ የኢንዱስትሪዎች እንዲሁም ባለሃብቶች ጋር በመቀናጀት ችግሩን ለመቅረፍ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢስት አፍሪካን ቦትሊንግ ኩባንያ ያከናወነው ግንባታም የዚሁ ጥረት ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።

ኩባንያው በድጋፍ ያበረከታቸው ሱቆች ለ36 ወጣቶች የስራ እድል የሚፈጥሩ ሲሆን የህዝብ መጸዳጃ ቤቱም ለ56 ቤተሰብ አባላት አገልግሎት ይሰጣል ብለዋል።

ከክፍለ ከተማው አመራር ጋር በመነጋገር በወረዳው ለበርካታ ጊዜያት ተዘግተው የቆዩ ሁለት ሼዶችን ለወጣቶች እንዲተላለፉ መደረጉንም ጨምረው ገልጸዋል።

ሸዶቹ ለ30 ወጣቶች የስራ እድል እንደሚፈጥሩም ነው ያብራሩት፡፡ 
በተጨማሪም ወጣቶች ተደራጅተው በአነስተኛ ክፍያ ለህብረተሰቡ የፎቶ ኮፒ አገልግሎት እንዲሰጡ ሁኔታዎች ተመቻችተዋል ብለዋል፡፡

የድጋፉ ተጠቃሚ ከሆኑ ወጣቶች መካከል ወጣት ዘነበች ወርቁ ከዚህ ቀደም በአረብ ሀገር በስደት እንደቆየችና እስካሁን ስራ እንዳልነበራት ገልፃ አሁን ግን የእድሉ ተጠቃሚ በመሆኗ ደስተኛ መሆኗን ተናግራለች።

ድጋፉን ላበረከቱልን አካላት ምስጋና ማቅረብ ያለብን ጠንክረን ሰርተን ውጤታማ በመሆን ነው ስትልም መልእክቷን አስተላልፋለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም