የተጀመረው የይቅርታና የዕርቅ ስራ ህዝባዊ መርህ ሊሆን ይገባል-የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ገባኤ

80
አዲስ አበባ  ሀምሌ 23/2010 የተጀመረው የይቅርታና ዕርቅ ስራ ህዝባዊና አገራዊ መርህ ሊሆን ይገባል ሲሉ የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ገባኤ አሳሰቡ። ተቋማቱ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት ማናጀር ኢንጅነር ስመኘው በቀለ ሞት የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘንም ገልፀዋል። የጉባኤው የበላይ ጠባቂ አባቶች በሀገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ መልዕክት አስተላልፈዋል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የበላይ ሃላፊ ብፁዕ አቡነ አረጋዊ  ለፕሮጀክቱ ውድ ጊዜያቸውንና ህይወታቸውን የሰጡ ስለነበሩ ተተኪው ትውልድ ግድቡን በርብርብ በማጠናቀቅ ልንክሳቸው ይገባል ብለዋል። የኢትዮጵያ አብያተ ክርስቲያናት ህብረት ፕሬዚዳንት ፓስተር ፃዲቁ አብዶ በበኩላቸው ስለ ግድያውም ፖሊስ አጣርቶ መረጃ እስኪሰጥ ከመላምት በመቆጠብ ሰላም አዋኪ ድርጊቶች እንዳይፈጠሩ ኃላፊነታችንን መወጣት እንደሚገባ አሳስበዋል። ለልጆቻቸው ተገቢውን ትምህርትና እንክብካቤ እንዲያገኙ በማድረግ ታሪክ ሰሪ እንዲሆኑ ኃላፊነታችንን  ልንወጣ ይገባልም ብለዋል። የኢትዮጵያ ኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የቦርድ አባል ሼህ ኡመር ኢማም ከቅራኔና ግጭት የሚገኝ ትርፍ ስለሌለ በኃይማኖትና ብሄር ስም የሚፈጠሩ ግጭቶች ለማስቆም ሁሉም በየአካባቢው መስራት አለበት ብለዋል። ግጭቶችን በእርቅና ይቅርታ ለመፍታት የተደረጉ ጅምሮች በሀገሪቱ የበለጠ እንዲጠናከሩ ሁሉም መስራት እንዳለበትም አሳስበዋል። የኃይማኖት ተቋማቱ የይቅርታውና እርቁ ስራ የህዝብና የሀገሪቱ አንድ መርህ ሆኖ መቀጠል አለበት ብለዋል። እርቅና ይቅርታ በኃይማኖትም የሚደገፍ በመሆኑ የኃይማኖት ተቋማቱ በበኩላችን ድጋፍ እናደርጋለን ብለዋል። የይቅርታ ስርዓቱ እንዳለ ሆኖ በሀገሪቱ የህግ የበላይነት እንዲከበርም በአፅንኦት መሰራት እንዳለበት ጠቁመዋል። በተለይም በሀገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች በብሄርና በኃይማኖት ሽፋን የሚከሰቱ ግጭቶች በተገቢው መንገድ መፈታት እንዳለባቸው በማውሳት። ግጭቶቹ እንዳይቀጥሉ የኃይማኖት ተቋማትና የሀገር ሽማግሌዎች የመከባበርና የመተሳሰብ ባህላችንን በማስተማር ሊሰሩበት ይገባል ብለዋል። በጌዲኦና ጉጂ አካባቢ በተከሰተው ግጭት የተፈናቀሉ ሰዎች ያሉበት ሁኔታ አሳሳቢ በመሆኑም ተገቢው እርዳታ ማድረግ እንዲሁም ወደነበሩበት ቦታ የመመለሱ ስራ በትኩረት መታየት እንዳለበትም ጠቁመዋል። የኃይማኖት ተቋማቱ ባላቸው የልማት ድርጅቶች አማካኝነት የበኩላቸውን ድጋፍ እንደሚያደርጉም አረጋግጠዋል። የኢትየጵያ መካነ ኢየሱስ ቤተ-ክርስቲያን፣ የኢትየጵያ ቃለ-ህይዎት ቤተ-ክርስቲያን፣ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ-ክርስቲያንና የኢትዮጵያ 7ኛው አድቬንቲስት ቤተ ክርስቲያናትም እርቅና ይቅርታን በሚያሰርጹ ተግባራት ላይ ጠንክረን መስራት አለብን በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም