የአካባቢያችንን ሰላም ለማስጠበቅ የድርሻችንን እንወጣለን -የጉጂ ኦሮሞ አባ ገዳዎችና ነዋሪዎች

49

ነገሌ ፣መጋቢት 28/2013 /ኢዜአ / የአካባቢያችንን ሰላም በማስጠበቅ የህግ የበላይነት እንዲከበር የድርሻችንን እንወጣለን ሲሉ የጉጂ ኦሮሞ አባ ገዳዎችና የነገሌ ከተማ ነዋሪዎች አስታወቁ፡፡

ሀዩ አባ ገዳ ሆኩ መገርሳ  ለኢዜአ እንደገለጹት በቂም በቀልና ጥላቻ ተነሳስቶ የግል ፍላጎትን ለማሳካት በሚደረግ ያልተገባ ተግባር ሀገር አይገነባም፤ ባህል አያድግም፤ ዘላቂ ሰላም አይመጣም፡፡

"በመሆኑም ሁሉም የአካባቢውን ሰላም በንቃት መከታተልና ፀረ ሰላም ሀይሎችን በማጋለጥ የድርሻቸውን መወጣት አለበት" ብለዋል።

የህግ የበላይነት ተከብሮ ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ ለሚሰማ ምክር በመስጠት፣ የተጣላን በማስታረቅና ለጥፋት የተሰማራን በማጋለጥ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል፡፡

የቀድሞ የጉጂ ኦሮሞ አባገዳ አባል አባሙርቲ ሳሙኤል ቦሩ "ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ ሁላችንም ከመንግስት ጋር ተባብረን የመስራት ግዴታ አለብን፣ እየሰራንም እንገኛለን"  ብለዋል፡፡

እርስ በእርስ መጠፋፋት ሀገር ከማፍረስ ባለፈ ማንንም አሸናፊ እንደማያደርግ ገልጸዋል፡፡

"መንግስት የህግ የበላይነትን በማስከበር እንዲሁም አባገዳዎች፣ የሀይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ደግሞ ህብረተሰቡን በማስተማር፣ ወጣቶችም በሰከነ መንፈስ በመንቀሳቀስ ዘላቂ ሰላም ማምጣት ይገባል" ብለዋል፡፡

 "የህግ የበላይነት ተከብሮ ሀገራችን ከተቃጣባት ችግር እንድትወጣ በሀገራችን ጉዳይ  ሁላችንንም ያገባናል፣ ለዚህም አካባቢያችንን በንቃት በመጠበቅ የድርሻችንን እየተወጣን ነው"  ያሉት ደግሞ የነገሌ ከተማ ነዋሪ አቶ ዘሪሁን አሰፋ ናቸው።

ህዝብና ሀገር ማስተዳደር የሚቻለው ሰላም ሲኖር በመሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ለሰላም ቅድሚያ ሰጥተው መንቀሳቀስ እንደሚገባቸው መክረዋል፡፡

የከተማው ነዋሪ ወጣት በዳዳ ሰመሎ ወጣቶች ሀገር የሚያፈርስ የጥፋት ሀይል ተባባሪና መሳሪያ ላለመሆን ነገሮችን በጥንቃቄ መከታተል እንዳለባቸው ጠቁሟል፡፡

የጉጂ ዞን ፖሊስ መምሪያ የኮሙኒኬሽን ዲቪዥን ሀላፊ  ምክትል ኮማንደር በቃሉ በለጠ ከዞኑ ህዝብና ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የህግ የበላይነት እንዲከበር ያላሰለሰ ጥረት በማድረግ ላይ እንደሆነ ገልጿል።

ባለፉት ዘጠኝ ወራት በዞኑ ህዝብ ጥቆማ ከ200 በላይ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ በቁጥጥር ስር መዋሉን አስታውሰዋል፡፡

ስንቅ በማቀበልና መንገድ በማሳየት የኦነግ ሸኔ የጥፋት ቡድን አባላት ተባባሪ የነበሩ 153 ተጠርጣሪዎች በህዝብ ጥቆማ ተይዘው በምክር መለቀቃቸውን ገልጸዋል፡፡

የህግ የበላይነት ተከብሮ ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ ፖሊስ ከተባባሪ ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የተጠናከረ ጥበቃ፣ ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ ላይ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም