በሐረሪ የተገኘው የሰው አጽም ለተጨማሪ ምርመራ ወደ ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል መላኩን ፖሊስ አስታወቀ

91
ሐረር ሐምሌ 23/2010 በሐረሪ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ቅጥር ግቢ የተገኘው የሰው ልጅ አጽም ለተጨማሪ ምርመራ ወደ አዲስ አባባ ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል መላኩን ፖሊስ አስታወቀ፡፡ እስካሁን በማህበራዊ ድህረ ገጾች  የዛሬ ሰባት ዓመት ሰው ተሰውረውብናል እየተባለ ከሚወራው ሌላ በተጨባጭ ግልጽ መረጃና አቤቱታ ያቀረበ እንደሌለ ተመልክቷል፡፡ በክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን የተቋቋመው የምርመራ ቡድን አስተባባሪ ምክትል ኮማንደር አብዱልዚዝ አብዱረሃማን ዛሬ እንደገለጹት የምርመራ ቡድኑ ለአስራ አንድ ቀናት አጽሙ ከየት እንደመጣ ምርመራ ሲያካሂድ ቆይቷል። በዚህም ምርመራ አብዛኛው አጽም በከተማው ልዩ ስሙ ሐማሬሳ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ለኢንዱስትሪ ልማት ስራ በተካሄደው ቁፋሮ ተገኝቶ እንደመጣ  በሰው ማስረጃ ማረጋገጥ መቻሉን ተናግረዋል፡፡ የተወሰነ አጽም ግን ከሸዋበር አካባቢ መጥቷል ቢባልም እስካሁን በማስረጃ አለመረጋገጡን አስተባባሪው ጠቁመው ለምን እንደመጣና እስካሁን መፍትሄ ያላገኘበት ምክንያት  ምርመራው ቀጥሎ እንደለ ገልጸዋል። ምክትል ኮማንደሩ እንዳመለከቱት በማህበራዊ ድህረ ገጾች የዛሬ ሰባት ዓመት ተሰውረውብናል እየተባለ ከሚወራው ሌላ እስካሁን ለምርመራ ቡድኑ በተጨባጭ ግልጽ መረጃና አቤቱታ ያቀረበ የለም፡፡ ሆኖም የሚነገሩት ወሬዎች ትክክለኛነት  ለማረጋገጥ ተጨማሪ ምርመራው በማስፈለጉ አጽሙ ትላንት ወደ ቅዱስ  ጳውሎስ ሆስፒታል መላኩን አስታውቀዋል። ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ እስካሁን ድረስ በቁጥጥር ስር የዋለ ግለሰብ አለመኖሩን ጠቁመው ነገር ግን አጽሙ በክብር መቀበር ሲገባው ይህን እንዳይሆን ያደረገው አካል ተጣርቶ በህግ እንደሚጠይቅም አስታውቀዋል። ህብረተሰቡም የምርመራው ስራ ተጠናቆ ይፋ እስከሚደረግ ድረስ በትግስት እንዲጠባበቅ ምክትል ኮማንደር አብዱላዚዝ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም