ለብሔራዊ ቡድኑ ተጨዋቾች ቀድሞ ጥሪ በማድረግ የውድድር ዝግጅት መደረጉ ለውጤቱ አስተዋጽኦ አድርጓል- አሰልጣኝ ውበቱ አባተ

91

አዲስ አበባ መጋቢት 27/2013  (ኢዜአ) ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ብሔራዊ ቡድኑ ተጨዋቾች ቀድሞ ጥሪ በማድረግ የውድድር ዝግጅት መደረጉ ለውጤቱ አስተዋጽኦ እንደነበረው አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ገለፀ።

በካሜሮን አስተናጋጅነት በሚካሄደው 33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ በምድብ ዘጠኝ የነበረችው ኢትዮጵያ ኮትዲቫዋርን ተከትላ በውድድሩ ላይ መሳተፏን አረጋግጣለች።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ውበቱ አባተ የብሔራዊ ቡድኑ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጉዞ አስመልክቶ ዛሬ ለመገናኛ ብዙሃን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

ለብሔራዊ ቡድኑ ተጨዋቾች ቀድሞ ጥሪ በማድርግ የውድድር ዝግጅት መደረጉ ለውጤቱ አስተዋጽኦ አድርጓል ብሏል።

በቀጣይም ክለቦችን በማይጎዳ መልኩ ተጫዋቾችን ቀድሞ ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግና ከክለቦች አሰልጣኖች ጋር ለብሔራዊ ቡድኑ በሚመረጡ ተጫዋቾች ላይ ውይይት ማድረግ እንደሚገባ ገልጿል። 

የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎቹ ብሔራዊ ቡድኑ በአፍሪካ ዋንጫ ለሚያደርገው ዝግጅት እግረ መንገዱን አቋሙን የሚፈትሽበት እንደሆነ አሰልጣኝ ውበቱ ተናግሯል። 

በተለይም ኢትዮጵያ ምድብ የሚገኙት ጋናና ዚምባቡዌ በአፍሪካ ዋንጫ ጭምር ተሳታፊ መሆናቸው ለቡድኑ  እንደ ጥሩ እድል የሚታይ ነው ብሏል። 

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ በ2013 ዓ.ም በምታስተናግደው የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ(ሴካፋ) ከ23 ዓመት በታች ውድድር ታዳጊ ተጫዋቾችን እንደሚያሰልፍ ነው አሰልጣኝ ውበቱ የገለጸው። 

ዋናው ብሔራዊ ቡድን ለአፍሪካ ዋንጫ እና ለዓለም ዋንጫ ማጣሪያ እንደሚዘጋጅ አመልክቷል። 

ይሄ ውሳኔ ብሔራዊ ቡድኑ ላይ የጨዋታ መደራረብ ጫና እንዳይፈጥርና ለታዳጊ ወጣቶች እድል መስጠትን ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ተናግሯል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአፍሪካ ዋንጫ ሲሳተፍ የካሜሮኑ የአፍሪካ ዋንጫ ለ11ኛ ጊዜ ሲሆን ቡድኑ ለመጨረሻ ጊዜ በአፍሪካ ዋንጫ የተሳተፈው እ.አ.አ በ2013 ደቡብ አፍሪካ ባስተናገደችው 29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ነበር።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም