በጉጂ ከ8ሺህ ሄክታር በላይ አዲስ መሬት ላይ የቡና ችግኝ ለመትከል ዝግጅት እየተደረገ ነው

211

ነገሌ መጋቢት 27/2013(ኢዜአ) በጉጂ ዞን በመጭው ክረምት ተጨማሪ 8ሺህ 100 ሄክታር መሬት ላይ የቡና ችግኝ ለመትከል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የዞኑ ግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

የጽህፈት ቤቱ ሀላፊ አቶ ታደሰ ብዙነህ ለኢዜአ እንደገለጹት በዞኑ የቡና ልማት ለማስፋፋት በክረምት ወቅት ለሚካሄድ አዲስ ተከላ 35 ሚሊዮን የቡና ችግኞች ተዘጋጅተዋል።

ችግኞቹ በመንግስት ጣቢያዎች የተዘጋጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የቡና ችግኞቹ  ከምርምር ማእከላት የወጡና ድርቅና በሽታን በመቋቋም ፈጥኖ ለምርት የመድረስ ባህሪ ያላቸው ዝርያዎች መሆናቸውን ተናግረዋል።

በተጨማሪም ዝርያዎቹ የተሻለ ምርት የመስጠት አቅም ያላቸው በመሆናቸው የቡና ምርታማነት መጠንና የጥራት ደረጃ ለማሻሻል አስተዋጾ  እንዳላቸው ጠቅሰዋል።

አዲስ የሚተከሉት የቡና ዝርያዎች ከነባሩ ዝርያ በሄክታር እየተገኘ ያለውን ሰባት ኩንታል ምርት ወደ ዘጠኝ ኩንታል ለማሳደግ አቅም ያላቸው መሆናቸውን አመልክተዋል።

በክረምቱ አዲስ በሚካሄደው የችግኝ ተከላ ለመሳተፍ እስካሁን የመሬት ዝግጅት ያደረጉ 15 ሺህ 384 አርሶ አደሮች 14 ሚሊዮን ጉድጓዶችን መቆፈራቸውን ተናግረዋል።

"በልማቱ ከሚሳተፉ አርሶ አደሮች መካከል 856ቱ ሴቶች ናቸው" ብለዋል፡፡

በዞኑ በ11 ወረዳወች በ126 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ እየለማ ካለው የቡና ተክል 80 በመቶው ምርት የሚሰጥ መሆኑን ገልጸዋል።

እንደ ሀላፊው ገለጻ በክረምቱ አዲስ በሚለማው መሬት አጠቃላይ የቡና ልማቱ ወደ 134 ሺህ 100 ሄክታር ያድጋል።

በዞኑ የአዶላ ሬዴ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ሀይሉ ገልገሎ በመጭው ክረምት በግማሽ ሄክታር አዲስ መሬት ላይ የቡና ችግኝ ለመትከል እየተዘጋጁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በተያዘው አመት ምርታማነትን የሚጨምር አዲስ የተሻሻለ የቡና ችግኝ ለማቅረብ ከመንግስት በተገባላቸው ቃል መሰረት ለተከላው ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል ።

ለሰብል ልማት ከሚጠቀሙበት ስድስት ሄክታር መሬት ሁለቱን ወደ ቡና ልማት ለመቀየር አቅደው ለችግኝ ተከላ የማሳ ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ  የወረዳው ነዋሪ አርሶ አደር ኢሳቅ አበራ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም