ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እስከሚጠናቀቅ ድጋፋቸውን እንደሚያጠናክሩ የመንግሥት ሠራተኞች ገለጹ

140

ሀዋሳ ፤መጋቢት 27/2013 (ኢዜአ) ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከዳር እስኪደርስ እያደረጉ ያሉትን ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የደቡብ ክልል  የመንግሥት ሠራተኞች ገለጹ።

 በደቡብ ክልል በተያዘው ዓመት እስከ የካቲት 30 ድረስ ከ35 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ መሰብሰቡ ታውቋል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል በክልሉ ምክር ቤት የሰው ሀብት ዳይሬክቶሬት ባለሙያ ወይዘሮ ታደለች ዮሐንስ የህዳሴው ግድብ ግንባታ የመሠረተ ድንጋይ ሲቀመጥ ለዘመናት የነበረውን የአይቻልም አመለካከት መስበሩን  አስታውሰዋል።

በዓባይ ወንዝ ዙሪያ ይነገሩ የነበሩ ጎታች  አስተሳሰቦችና ትርክቶች ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ማስቀረት  መቻሉንም ተናግረዋል።

እሳቸውም ለግድቡ  ያላቸውን ድጋፍ በመግለጽ  ቦንድ በመግዛት አጋርነታቸውን በተግባር በማስመስከር ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በሁላችንም ተሳትፎና ትብብር ለዚህ ደረጃ ያበቃነውን ግድብ መጨረስ አይከብደንም ያሉት ወይዘሮ ታደለች የውስጥና የውጭ ተፅዕኖን በመቋቋም ግድቡን በማጠናቀቅ ድል ማድረግ እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።

ለሶስተኛ ጊዜ የአንድ ወር ደመወዛቸውን ለግድቡ ድጋፍ እንዲውል የቦንድ ግዢ መፈጸማቸውን ጠቅሰዋል።

በክልሉ የዳያስፖራ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ባለሙያ ወይዘሮ ፍሬወርቅ ተሾመ በበኩላቸው የግድቡ ሥራ ባጋጠመው ክፍተትና ምዝበራ ምክንያት ተሳትፏችን በመሀል ተቀዛቅዞ የነበረ ቢሆንም የተወሰደው የማስተካከያ እርምጃና አሁን የደረሰበት ደረጃ ሁሉንም ህብረተሰብ ዳግም ያነቃቃ ነው ብለዋል።

ግድቡ እየተገነባ ያለው የሌሎች ሀገራትን ጥቅም በማይጎዳ መልኩ እንደሆነ ጠቅሰው በብዙ ተግዳሮት ውስጥ ያሉ ወገኖቻችንን ችግር የሚፈታ በመሆኑ  ለግድቡ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው መቀጠላቸውን ገልጸዋል።

የህዳሴው ግድብ ለቀጣዩ ትውልድ የምናስረክበው የአንድነታችን አሻራ ያረፈበት ነው ያሉት ወይዘሮ ፍሬወርቅ  ስራው እስኪጠናቀቅ ድረስ የሚጠበቅባቸውን ማንኛውም አስተዋፅኦ ለማበርከት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል

አሁን ላይ ለአራተኛ ጊዜ የአንድ ወር ደመወዛቸውን ለቦንድ ግዢ ለማዋል  በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ለግድቡ ድጋፍ እንዲውል ለስድስተኛ ጊዜ በአንድ ወር ደመወዛቸው ቦንድ መግዛታቸውን የተናገሩት ደግሞ የክልሉ የብሔረሰቦች ምክር ቤት ባለሙያ አቶ አሻግሬ አሰፋ ናቸው።

የህዳሴው ግድብ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ለአንድ ዓላማ ያስተባበረ ፕሮጀክት ነው ያሉት አቶ አሻግሬ በቀጣይም በግድቡ ዙሪያ ከውጭም ሆነ ከውስጥ ተላላኪዎች የሚቃጡ ማንኛውም ጥቃቶች በጋራ መመከት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያዊያን በገንዘባቸውና በዲፕሎማሲው መስክ እያደረጉ ያሉት ርብርብ በተለይ የግብፅን ተፅዕኖ ለመመከት ትልቅ አንድምታ ያለው እንደሆነ ገልፀው አሁን ላይ ያለው መነቃቃት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል።

የደቡብ ክልል የታላቁ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ዳይሬክተር አቶ ሚልኪያስ እስራኤል እንዳሉት፤ ከለውጡ ወዲህ በግድቡ ግንባታ ላይ የታየው ተጨባጭ ለውጥ  ህዝባዊ አጋርነቱና ወገንተኝነት እንዲጨምር አድርጓል።

በተያዘው ዓመት ደግሞ እስከ የካቲት 30 ድረስ ከቦንድ ሽያጭ ፣ ከዚህ በፊት ቃል ከተገባ ገንዘብና ከሌሎች ገቢዎች ከ35 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ መሰብሰቡን አስታውቀዋል።

አሁን ላይ በክልሉ ሰፊ የተሳትፎ መነቃቃት መኖሩን የገለጹት  አቶ ሚልኪያስ ይህንን ምቹ አጋጣሚ በመጠቀም የተለያዩ የንቅናቄ ሥራዎችን እየሰራን ነው ብለዋል።

እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ በክልሉ ባሉ ከተሞች ከመጋቢት 21 ጀምሮ ለ10 ቀናት ሚቆይ የቦንድ ሽያጭ ንቅናቄ እየተካሄደ ይገኛል።

በደቡብ ክልል ባለፉት አስር ዓመታት ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች  የዓይነት ሳይጨምር  በቦንድ ግዢና ልገሳ ከ1 ቢሊዮን  200 ሚሊዮን  ብር በላይ በመሰብሰብ ድጋፍ መደረጉን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም