በአማራ ክልል በዘመናዊ መስኖ እየለማ ያለው መሬት ከ105 ሺህ ሄክታር አይበልጥም...ቢሮው

106

ባህር ዳር ፤መጋቢት 27/2013 (ኢዜአ ) በአማራ ክልል በዘመናዊ መስኖ መልማት ከሚችለው መሬት ውስጥ እስካሁን 105ሺህ ሄክታሩ ብቻ ጥቅም ላይ መዋሉን የክልሉ ውሃ፣ መስኖና ኢነርጅ ልማት ቢሮ አስታወቀ።

በክልሉ በዘመናዊ መንገድ የሚለማውን መሬት ወደ አንድ ሚሊዮን ሄክታር ለማድረስ የተቋማት ግንባታ እየተካሄደ መሆኑ ተመልክቷል።

በአዊ ዞን ዳንግላ ወረዳ ውምብሪት ቀበሌ 800 ሄክታር መሬት የሚያለማ የውብሪ መስኖ ልማት ፕሮጀክት መልሶ የማስጀመር ስራ ትናንት ተከናውኗል።

የቢሮው ምክትል ሃላፊ አቶ መለሰ ስንትአየሁ በስነ ስርዓቱ ላይ እንዳሉት ክልሉ ባለው የውሃ ፀጋና መልማት በሚችለው መሬት ልክ እየለማ አይደለም።

በክልሉ በመስኖ መልማት የሚችል 2 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሄክታር መሬትና ከ40 እስከ 60 ቢሊዮን ሜትር ኩብ አመታዊ የውሃ አቅም መኖሩን ተናግረዋል ።

ካለው የውሃ መጠንና መልማት ከሚችለው መሬት ውስጥ እስካሁን ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው ከ5 በመቶ የማይበልጥ እንደሆነ አመልክተዋል።

ባለፉት ዓመታት ዘርፉን ለማሻሻል በተደረገ እንቅስቃሴ 590 የመስኖ ተቋማት በመገንባት 105 ሺህ ሄክታር መሬት በዘመናዊ መስኖ ማልማት መቻሉን ጠቅሰዋል።

አሁን ላይ 122 የመስኖ ተቋማት በግንባታና በጥገና ላይ እንደሚገኙ ያብራሩት ምክትል ሃላፊው "የተቋማቱ ግንባታ ተጠናቆ ወደ አገልግሎት ሲገቡ የሚለማውን የመሬት ሽፋን 50 በመቶ ማሳደግ ይችላል" ብለዋል።

በግንባታ ላይ ካሉ ትላልቅ የመስኖ ፕሮጀክቶች መካከል ርብ፣ መገጭ፣ ግልገል አባይ፣ አጅማ ጫጫ፣ ላይኛው ርብ፣ ጀማ ፈዘዝና ብር ጭምብል እንደሚገኙበት አመልክተዋል።

የሽንፋ መስኖ ፕሮጀክት የጥናት ስራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

በቀጣይ አምስት ዓመት በግንባታ ላይ ያሉትን ጨምሮ ሌሎች የመስኖ ፕሮጀክቶችን አጠናቆ ወደ ልማት በማስገባት የሚለማውን መሬት ወደ አንድ ሚሊዮን ሄክታር ለማሳደግ ታስቦ እየተሰራ እንደሆነ አብራርተዋል።

ለመስኖ ፕሮጀክቶች ግንባታ ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት ተመድቦ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው "የውንብሪ መስኖ ፕሮጀክት የዚሁ አካል ሆኖ በ95 ሚሊዮን ብር ግንባታው መልሶ ተጀምሯል" ብለዋል።

በጥናት ችግር፣ ተቀናጅቶ በስራት ክፍተትና በተቋራጮች አቅም ችግር ግንባታዎች ተጀምረው የመቋረጥ ክፍተት እንዳለ አመልክተው ችግሩን ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን አቶ መለሰ አስታውቀዋል።

የአዊ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ባይነሳኝ ዘሪሁን በበኩላቸው የውንብሪ የመስኖ ፕሮጀክት 800 ሄክታር መሬት የማልማት አቅም ያለው መሆኑን ተናግረዋል።

የመስኖ ፕሮጀክቱ ከስድስት ዓመት በፊት ስራው ቢጀመርም በተቋራጭ አቅም ማነስ  ተቋርጦ ቆይቶ በአዲስ መልክ መጀመሩን ተናግረዋል።

ፕሮጀክቱ በዞኑ በግንባታ ላይ ከሚገኙ 12 የመስኖ ፕሮጀክቶች ትልቁ እንደሆነ ጠቅሰው ከ4 ሺህ ያላነሱ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

የፕሮጀክቱ ስራ መቋረጥ በአካበቢው አርሶ አደር ዘንድ የመልካም አስተዳደር ችግር ፈጥሮ መቆየቱን ጠቁመው አሁን ላይ የተጀመረው ስራው በተገባለት ውል መሰረት ተጠናቆ ለአገልግሎት እንዲበቃ አስፈላጊው ክትትልና ድጋፍ እንደሚደረግ አስታውቀዋል።

የፕሮጀክቱን ግንባታ የተረከቡት ዘውዱ ወንድ ይፍራው ጠቅላላ የውሃ ተቋራጭና የድርጅቱ ስራ አስኪያጅ አቶ ዘውዱ ወንድ ይፍራው በበኩላቸው "ህብረተሰቡ በጉጉት የሚጠብቀው የመስኖ ግድብ በተያዘለት ጊዜ ጥራቱን ጠብቆ እንዲጠናቀቅ በቁርጠኝነት እንሰራለን" ብለዋል።

ፕሮጀክቱን በተያዘለት ጊዜ ለማጠናቀቅ  በቂ የሰው ሃይልና ማሽን መቅረቡን ጠቁመው የአካባቢው ማህበረሰብና አስተዳደር ወሰን በማስከበር ተገቢውን እገዛና ትብብር እንዲያደረግ ጠይቀዋል።

የመስኖ ፕሮጀክቱ ተጀምሮ በመቋረጡ  አዝነው እንደነበር ያስታወሱትና አሁን ስራው በመጀመሩ መደሰታቸውን የገለፁት ደግሞ የውምብሪት ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ስንታየሁ ጌጡ ናቸው።

የመስኖ ፕሮጀክቱ በተያዘለት ጊዜ ተጠናቆ ለአገልግሎት እንዲበቃ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል።

በውንብሪ አነስተኛ መስኖ ፕሮጀክት መልሶ ማስጀመር ስነ ስርዓት ላይ የክልሉና የዞኑ አመራሮች እንዲሁም የአካባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም