በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ አቅመ ደካሞችና ሴቶችና ወጣቶች የመኖሪያ ቤትና የመስሪያ ሼድ ተሰጣቸው

87

መጋቢት 26/2013 (ኢየአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ 85 አቅመ ደካሞች የመኖሪያ ቤቶች እና 770 ሴቶች እና ወጣቶችን ተጠቃሚ የሚያደርግ 166 የመስሪያ ቦታ ሼዶችን አስረከበ።

በመርሃ-ግብሩ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ እንደገለፁት፤ የከተማዋ ሀብት በእኩልነት እና በፍትሃዊነት ለህዝቡ ለማድረስ የተጀመረው ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል።

የተጀመረው የልማት እና የብልጽግና ጉዞ እውን እንዲሆን ሁሉም በእኩል መተጋገዝ ይገባዋል ብለዋል።

በከተማ ውስጥ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች የስራ እድል እንዲፈጠር እንዲሁም የመኖሪያ ቤት ችግርን ለመፍታት ሲሰራ መቆየቱን አስታውቀዋል።

አሁን የተሰጠው የመኖሪያ ቤት የቁልፍ ርክክብ በህገ ወጥ መንገድ ተይዞ የነበረ ቤትና መሬት መሆኑን ገልጸው፤  ህገ-ወጥነትን በመጠየፍ  በማጋለጥ ዜጎች እኩል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማደረግ ነው ብለዋል።

በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የተሰራው ስራ የሚያስመሰግንና ሌሎች ሊከተሉት የሚገባ ተግባር ነው ሲሉም ተናግረዋል።

ሁሉንም በፍትሃዊነት ማገልገል ካልተቻላ ዘላቂ ልማትና ዕድገትና ሰላም ሊኖር እንደማይችል ገልጸው፤ ህዝቦች በአብሮነትና፤ በመደጋጋፍ፤ በመተባበር ከሰሩ የጋራ ተጠቃሚነት ማጉላት እንደሚችሉ ገልጸዋል።

የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈፃሚ ወይዘሮ ነጻነት ዳባ በበኩላቸው፤ በክፍለ ከተማው በህገወጥ መንገድ ተይዘው የነበሩ የመንግስት ቤቶችን በማስለቀቅ 85 ያህሉን በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ውስጥ ለሚገኙ አቅመ ደካሞች እና አካል ጉዳተኞች እንዲተላላፍ  መደረጉን አስታውቀዋል።


እንዲሁም ለረጅም አመታት ተደራጅተው የመስሪያ ቦታ ሼድ ለመውሰድ ሲጠባበቁ ለቆዩ በ181 ኢንተርፕራይዞች የተደራጁ 770 ሴቶች እና ወጣቶችን ተጠቃሚ የሚያደርግ 166 የመስሪያ ቦታ በዕጣ  ለዕድለኞች ተሰጥቷል።

ዕድለኞቹ በከተማ ውስጥ ያለውን የስራ አጥ ቁጥር ለመቀነስ በአንድነት መስራት እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም