በህዳሴው ግድብ መልማት በሚችሉ አማራጮች ላይ ለሚካሄዱ ምርምሮች ትኩረት ተሰጥቷል - አሶሳ ዩኒቨርሲቲ

107

መጋቢት 26 / 2013 (ኢዜአ) በህዳሴው ግድብ መልማት በሚችሉ አማራጮች ላይ ያተኮሩ ጥናትና ምርምሮችን እያካሄደ መሆኑን አሶሳ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ።

ዩኒቨርሲቲው “ምርምር ለምርትና ምርታማነት” በሚል መሪ ሀሳብ ያዘጋጀው የምርምር አውደ ጥናት በአሶሳ ከተማ ተካሂዷል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ሃይማኖት ዲሳሳ በወቅቱ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው የህዳሴው ግድብ ሃይል ማመንጨት ሲጀምር በሚኖሩ የልማት አማራጮች ላይ ከወዲሁ ትኩረት በማድረግ ጥናትና ምርምር እያካሄደ ነው፡፡

ዩኒቨርሲቲው  በጥናትና ምርምር ትኩረት ካደረገባቸው ዘርፎች መካከል የግድቡ ሃይቅ ለዓሳ ምርትና ተያያዥ ጉዳዮች የሚኖረውን ጠቀሜታ የተመለከቱ እንደሚገኙበት ጠቁመዋል፡፡

በግድቡ አካባቢ በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ የሚከናወኑ ተግባራት ሌላው  በጥናትና ምርምር ትኩረት የተደረገበት ዘርፍ መሆኑን ለአብነት ጠቅሰዋል።

በዩኒቨርሲቲው አሁን ላይ ዘርፎቹ የሚለሙበትን መንገድና አማራጭ ዘዴዎችን የሚመለከቱ ጥናትና ምርምሮች እየተካሄዱ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ከህዳሴ ግድብ በተጓዳኝ በክልሉ እምቅ የማዕድን ሃብት ጥቅም ላይ በሚውልበት መንገድና የግብርና ኢንቨስትመንት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በሚደገፍበት ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ጥናትና ምርምሮች እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል ።

ዩኒቨርሲቲው ጥናትና ምርምሮችን ወደ መሬት በማውረድ ረገድ የሚታዩ የባለድርሻ አካላት ቅንጅት ማነስ ክፍተቶችን ለመፍታት እየሠራ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

"በዘርፉ የረዥም ዓመት ልምድ ካላቸው የሃገር ውስጥ ዩኒቨርሲቲዎች ተሞክሮ እየተወሰደ ይገኛል" ብለዋል፡፡

በምርምር አውደ ጥናቱ ከተሳተፉት መካከል በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ የጂኦሎጂ ትምህርት ክፍል መምህርት ሳምራዊት ይማም እንዳሉት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ወርቅ በአብዛኛው በባህላዊ መንገድ ይመረታል።

"አብዛኞቹ በባህላዊ ወርቅ አምራቾች ደግሞ ሴቶች ናቸው" ብለዋል፡፡

"የዘርፉን ችግሮች በጥናትና ምርምር በማስደገፍ የምርት ሂደቱን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ እንዲታገዝ ማድረግ ያስፈልጋል " ያሉት መምህርቷ፤ በዘርፉ የሚካሄድ ጥናትና ምርምር የሴቶችን ጫና ከማቃለል በላይ ለሃገር ኢኮኖሚ ድርሻው የጎላ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

በምርምርና ጥናት ዘርፍ የሴቶችን ተሳትፎ ማሳደግ ሌላው ቀጣዩ ዩኒቨርሲቲው የሚጠበቅበት ስራ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

"በአውደ ጥናቱ  ከሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች የጥናትና ምርምር ልምድ አግኝተናል" በማለትም መምህርት ሳምራዊት አስታውቀዋል፡፡

በአውደ ጥናቱ  100 የሚሆኑ ምሁራንና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም