በአፋር እድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች ለሆኑ ህጻናት የልጅነት ልምሻ መከላከያ ክትባት መሰጠት ጀመረ

47

መጋቢት 26/2013 (ኢዜአ) በአፋር ክልል እድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች ለሆኑ ህጻናት የልጅነት ልምሻ መከላከያ ክትባት ዛሬ በሰጠት ጀመረ።

ክትባቱ  ከዛሬ ጀምሮ ለአራት ቀን ከ292 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ህጻናት በቤት ለቤት እንደሚሰጥ  የክልሉ ጤና ቢሮ ለኢዜአ አስታውቋል ።

በክልሉ ጤና ቢሮ የህጻናት ክትባት ንኡስ ስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ አወል ጉደሌ እንደገለጹት  ክትባቱ በሁሉም የክልሉ ወረዳዎች ይሰጣል ።

እድሜያቸው ከአምስት በአመት በታች ለሆኑ ከ292 ሺህ 437 በላይ ለሚሆኑ ህጻናት ክትባቱ እንደሚሰጥ ተናግረዋል ።

ክትባቱ ከሚሰጣቸው ህጻናት ውስጥ 6ሺህ 421 የሚሆኑት  በአይሳኢታና በራህሌ የኤርትራ ስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች  የሚገኙ መሆናቸውን አመልክተዋል።

ክትባቱን ከእድሜ ክልሉ በታች ለሆኑ ሁሉም ህጻናት ተደራሽ ለማድረግ ከመድሀኒት አቅርባትና ባለሙያ ጀምሮ በቂ ዝግጅት መደረጉን አስታውቀዋል።

ህብረተሰቡ ልጆቹን በማስከተብ ከአካል ጉዳተኝነት እንዲታደግም ጥሪ አቅርበዋል ።

በክልሉና አጎራባች በሆነው በአማራ ክልል ኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን  ከዚህ ቀደም በቫይረሱ የተጠቁ ህጻናት መገኘታቸውን ተከትሎ በህዳር 2013 ዓ.ም ከአማራ ክልል አጎራባች በሆኑ  አውሲ-ረሱ፣ ገቢ-ረሱና ሀሪ-ረሱ የአፋር ዞኖች ክትባቱ በዘመቻ መሰጠቱን አስታውሰዋል ።

እንደ አስተባባሪው ገለጻ በክልሉ ዛሬ የተጀመረው ክትባት በመደበኛ መርሀ ግብር የሚሰጥ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም