በአይሳኢታና በራህሌ ስደተኛ መጠለያዎች የድጋፍና መሰረተ ልማት አቅርቦት ክፍተቶች ለመፍታት ይሰራል-- ኤጀንሲው

68

ሰመራ መጋቢት 26 /2013 (ኢዜአ)-በአፋር ክልል አይሳኢታና በራህሌ የስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች የድጋፍና መሰረተ ልማት አቅርቦት ክፍተቶችን ለመፍታት ባለድርሻዎችን በማሳተፍ እንደሚሰራ ስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ኤጀንሲ አስታወቀ።

የኤጀንሲው  ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች በአይሳኢታ ስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ከስደተኛ ተወካዮችና ሠራተኞች ጋር ትላንት ተወያይተዋል።

የፌደራል ስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ አስተዳደር ኤጄንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ በወቅቱ እንደገለጹት ኢትዮጵያ በ27 መጠለያ ጣቢያዎች  ከተለያዩ ሀገራት የመጡ ከ1ሚሊዮን በላይ ስደተኞችን እያስተናገደች ትገኛለች።

ኤጀንሲው  የስደተኛ ጣቢያዎቹን  በአምስት ዞኖች ከፋፍሎ እያስተዳደረ መሆኑን ጠቁመው ከዞኖቹ አንዱ ሰመራ መሆኑን ጠቅሰዋል ።

በሰመራ ዞን ውስጥ በሚገኙ የበራህሌና አይሳኢታ ስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች  ከ60 ሺህ በላይ የኤርትራ ስደተኖች መኖራቸውን አመልክተዋል።

በመጠለያ ጣቢያዎቹና በዞኑ ያለውን የስደተኞች አያያዝና አጠቃላይ የድጋፍ  ክፍተቶች ለይቶ በማወቅ በአጭርና ረዥም ጊዜ ለመፍታት ጉብኝት አየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በዞኑ በሚገኙ ጣቢያዎች የመብራትና ውሃ አቅርቦት እንዲሁም ተያያዥ የስደተኛ ጉዳዮች አስተዳደር ከሌሎች ዞኖች አኳያ ሲታይ ሰፊ የመሠረተ-ልማት ክፍተቶች ያሉበት መሆኑን ጠቁመዋል።

በዞኑ ባሉ የስደተኛ ጣቢያዎች የመሠረተ-ልማት ችግሮች ለመፍታት ከባለድርሻዎች ጋር በትብብር እንደሚሰራ አመላክተዋል ።

ከአካባቢው ህብረተሰብ ጋር በመሠረተ-ልማትና በስራ እድል ፈጠራ የበለጠ ለማስተሳሰር የሚያግዙ ፕሮጀክቶች በመንደፍ ከተለያዩ መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ባለድርሻዎችጋር በቅንጅት እንደሚሰራ አስታውቀዋል። 

በአይሳኢታ ስደተኞች ጣቢያ የስደተኞች ተወካይ አቶ አብደላ መሀመድ በመጠለያ ጠቢያው የውሀ፣ ትምህርትና የጤና አገልግሎት አቅርቦት ላይ ክፍተት መኖሩን ጠቁመዋል።

የምግብና ምግብነክ ድጋፎችም በቂ አለመሆናቸውንና ወቅቱን ጠብቀው እየቀረቡ እንዳልሆነም አመልክተዋል።

በጣቢያው ከ25 ሺህ በላይ ስደተኞች እንደሚገኙና ከቁጥራቸው አንጻር በቂ መጠለያና ማህበራዊ አገልግሎት አለመኖሩን የገለጹት ደግሞ  የጣቢያው ተጠሪ አቶ መሀመድ ሁመድ ናቸው።

በጣቢያው ያለው የድጋፍና የአገልግሎት አቅርቦት ክፍተት እንዲፈታላቸው ጠይቀዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም