ዲስትሪክቱ በአንድ ሳምንት ከ700 ሺህ በላይ የአሜሪካ ዶላር መነዘረ - ኢዜአ አማርኛ
ዲስትሪክቱ በአንድ ሳምንት ከ700 ሺህ በላይ የአሜሪካ ዶላር መነዘረ
171
ባህር ዳር 23/2010 የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባህር ዳር ዲስትሪክት በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ከ700 ሺህ በላይ የአሜሪካ ዶላር መመንዘሩን አስታወቀ። የዲስትሪክቱ ዳይሬክተር አቶ ዮሴፍ ዓለማየሁ ለኢዜአ እንደገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የውጪ አገር ገንዘቦችን በቤታቸው ያስቀመጡ ግለሰቦች ወደ ባንክ አምጥተው እንዲመነዝሩ ያስተላለፉትን ጥሪ ተከትሎ በዲስትሪክቱ ስር በሚገኙ ባንኮች እየተመነዘረ ያለው የዶላር መጠን እየጨመረ ነው። በዲስትሪክቱ ስር ባሉ 81 ቅርንጫፎች በቀን በአማካኝ ከ110 ሺህ ዶላር በላይ እየተዘረዘረ መሆኑን የገለጹት ዳይሬክተሩ ቀደም ሲል ይመነዘር የነበረው በአማካኝ ከ500 ዶላር ይበልጥ እንዳልነበር አስታውሰዋል። " በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ብቻ በዲስትሪክቱ ሥር ባሉ ባንኮች 704 ሺህ 301 የአሜሪካ ዶላር ተዘርዝሯል " ብለዋል ። ብዙ የዶላር ክምችት ያላቸው ሰዎች በአንድ ጊዜ ወደ ባንክ ካመጣን እንጠየቃለን በሚል ስጋት ገንዘባቸውን እየቀናነሱ የሚያመጡበት ሁኔታ መስተዋሉንም ጠቁመዋል ። ይሁንና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባስተላለፉት መልክት መሰረት ማንኛውም ግለሰብ በተሰጠው ጊዜ ውስጥ የፈለገውን የዶላር መጠን ወደ ሚቀርበው ባንክ በማምጣት ምንጩ ሳይጠየቅ መመንዘር እንደሚችል ገልፀዋል። በእጃቸው የዶላር ክምችት ያላቸው ሰዎች በተሰጠው ጊዜ ውስጥ ካልመነዘሩ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተላለፉ እርምጃዎች ሊጠብቋቸው እንደሚችሉም አቶ ዮሴፍ አመልክተዋል። ዶላር ይዘው የሚመጡ ደንበኞችም በባንኩ በልዩ ሁኔታ እየተስተናገዱ መሆናቸውንም አቶ ዮሴፍ አስታውቀዋል።