አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ የአርባምንጭ እግር ኳስ ክለብ አሰልጣኝ ሆነው ተሹመዋል

117
አዲስ አበባ ሀምሌ 23/2010 አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ በዘንድሮው ዓመት ከፕሪሚየር ሊጉ የወረደው የአርባምንጭ እግር ኳስ ክለብ አሰልጣኝ ሆነው ተሹሟል። በክለቡ ለአንድ ዓመት ለማሰልጠን የኮንትራት ውል መፈራረማቸውን ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ገልጿል። አርባ ምንጭ ከተማ እግር ኳስ ክለብ በዘንድሮው ዓመት ፕሪሚየር ሊግ 33 ነጥብ ይዞ 15ኛ ደረጃን በመያዝ ከፕሪሚየር ሊጉ መውረዱ ይታወቃል። ወደ ከፍተኛ ሊግ የወረደውን የአርባ ምንጭ ከተማ እግር ኳስ ክለብ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ በድጋሚ እንዲመለስ ለማድረግ እንደሚሰራም ተናግሯል። በከፍተኛ ሊግ ያለው ፉክክር በጣም ፈታኝ ቢሆንም ከሁሉም አካላት ጋር በጥምረት ከተሰራ ክለቡ ወደ ፕሪሚየር ሊግ የማይመለስበት ምንም አይነት ምክንያት አይኖርምም ብሏል አሰልጣኝ መሳይ። በቀድሞው የአርባ ምንጭ ጨርቃ ጨርቅ ክለብ ተጫዋች ሆነው ያሳለፉት አሰልጣኝ መሳይ ቡድኑን በአሰልጣኝነት መረከቡን እንደ መልካም አጋጣሚ እንደሚያይም አመልክቷል። በቀጣይ ከክለቡ ተጫዋቾች ጋር ውይይት እንደሚያደርግና የነባር ተጫዋቾች ቆይታና ወጣት ተጫዋቾችን ከታች የማሳደግ ሁኔታ ላይም ትኩረት ሰጥተው እንደሚሰራ ነው አሰልጣኝ መሳይ የተናገረው። ክለቡ በከፍተኛ ሊግ ጠንካራና ተወዳዳሪ ሆኖ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ እንዲሚለስ ለክለቡ ይመጥናሉ የሚሏቸውን ተጫዋቾች ለማስፈረም እቅድ እንዳለውም ገልጸዋል። የክለቡን ተጫዋቾች በአካል ብቃትና በስነ ልቦና ዝግጁ አድርጎ በጠንካራ መንፈስ እንዲጫወቱ የማድረግ ስራ ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው እንደሆነም አክሏል። በ2010 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የውድድር አጋማሽ ፋሲል ከተማን ተረክቦ ሲያሰለጥን የነበረው አሰልጣኝ መሳይ ሰኔ 30 ቀን 2010 ዓ.ም የኮንትራት ውሉ መጠናቀቁን ተከትሎ ከክለቡ ጋር መለያየቱ የሚታወስ ነው። አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ከፋሲል ከተማ በፊት ወላይታ ዲቻን ለዘጠኝ ዓመት በአሰልጣኝነት መርቷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም