የትውልዶች የጋራ አሻራ

107

በመንግስቱ ዘውዴ (ኢዜአ)

የአባይን ልጅ ውሃ ጠማው እንዲል ምሳሌው የኢትዮጵያ ህዝቦች የአባይ ወንዝ በጥቅም ላይ ውሎ ሀገራቸውን እራትም መብራትም ሆኖ እንዲያለማላቸው ለዘመናት ሲመኙ ኖረዋል፡፡

ምንም እንኳን ኢትዮጵያ የአባይን ወንዝ እንዳትጠቀም የሚያግዳት ህግ ባይኖርም በተለያዩ ምክንያቶች ለዓመታት ሳትጠቀምበት ቆይታለች፡፡እንግሊዝ የሰሜናዊና የምስራቅ አፍሪካ ሀገራትን በቅኝ ግዛት ከያዘች በኋላ በግብጽ ከፍተኛ የጥጥ እና ሌሎችም ልማቶችን ማካሄድ ጀምራ ስለነበር እ.አ.አ በ1929 ወደ ግብጽ የሚደርሰውን የአባይን ውሃ መጠን የሚቀንስ ማንኛውም ተግባር በወንዙ ላይ እንዳይከናወን ደንግጋለች።

በዚህ ስምምነት መሰረት ግብፅ በዓመት 48 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ስታገኝ ሱዳን 4 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ብቻ እንዲደርሳት ተደርጎ ነበር፡፡ ሁለቱ ሀገራት ከእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ነጻ ከወጡ በኋላ እ.ኤ.አ በ1959 ዓ.ም በተዋዋሉት አዲስ ስምምነት ግብጽ በዓመት 55 ነጥብ 5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ሱዳን ደግሞ 18 ነጥብ 5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ መጠቀም የሚያስችላቸውን ሰነድ ተፈራርመዋል።

ኢትዮጵያን ያገለለው ይህ ኢፍትሃዊ የአባይ ውሃ አጠቃቀም ህዝቡን ለዘመናት እያንገበገበው አንዴ በዜማ ሌላ ጊዜ በስነ-ጽሁፍ ውስጣዊ ቁጭታቸውን ሲገልጹ ቆይተዋል።የኢፌዴሪ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ሲለሺ በቀለ በአንድ ወቅት በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን “የእኛ ጉዳይ” ፕሮግራም ላይ እንዳብራሩት ኢትዮጵያ ከ1950ዎቹ ጀምሮ የአባይን ወንዝ ለኤሌክትሪክ ሀይል እና ለሌሎች ልማቶች ለመጠቀም ፍላጎቱ የነበራት ቢሆንም በአንድ በኩል በውስጣዊ አቅም ውስንነት በሌላ በኩል ግብጽ የዓለም የገንዘብ ተቋማት እርዳታና ብድር እንዳይሰጡ ሲያግባቡ በመቆየታቸው ጥቅም ላይ ማዋል አለመቻሉን አብራርተዋል።

ይህ የዘመናት የህዝቦች ጥያቄና ቁጭት መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጉባ ወረዳ በተጣለው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመሰረት ድንጋይ ወደ አዲስ ምእራፍ ተሸጋገረ። በዚህ ወቅት የፕሮጀክቱን መጀመር ያበሰሩት የቀድሞው የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ግብጽ ከነበራት ተጽእኖ አንፃር እርዳታና ብድርን አማራጭ ብናደርግ እስከመቼም ድረስ የአባይን ወንዝ ለልማት ማዋል አንችልም በማለት ነበር የገለጹት።

በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልእክት “የግድቡ ባለቤቶች እኛው፣ መሀንዲሶቹም እኛው፣ የገንዘብ ምንጩም እኛው ነን” በማለት ግድቡን ኢትዮጵያውያን በራሳቸው አቅም እንደሚሰሩት አረጋግጠዋል።ፕሮጀክቱን እውን ለማድረግ ህዝቡ በይቻላል መንፈስ ንቅናቄ መፍጠር እንዳለበት የቀረበውን ጥሪ ተከትሎ በሀገራችን የልማት ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ የህዝብ ድጋፍና ተሳትፎ የተንጸባረቀበት ታሪካዊ ፕሮጀክት ለመሆን ችሏል።

የግድቡ ግንባታ ከተበሰረበት ጊዜ ጀምሮ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት የሚገኘው መላው የሀገራችን ህዝብ ከልጅ እስከ አዋቂ፣ ከተማሪ እስከ ምሁር፣ ከደሃ እስከ ባለሀብት፣ የኢትዮጵያ ልጆች ያለምንም የብሄር፣ የሃይማኖት፣ የጾታና የገቢ ልዩነት በደማቅ የድጋፍ ሰልፎች በማጀብ፣ ቦንድ በመግዛት፣ ስጦታ በማበርከት ከፍተኛ ርብርብ አድርገዋል፤ እያደረጉም ይገኛል።

ኢትዮጵያ በህዝቦቿ አቅም ያለምንም የውጭ እርዳታና ብድር እየገነባችው ያለው የህዳሴው ግድብ ከግብጽ እና ሱዳን ጋር መተማመንን ለመፍጠር እና ትብብርን ለማጠናከር ረጅም ርቀት ተጉዛለች፡፡ የግድቡ መገንባት የወንዙን የውሃ ፍሰት መጠን እንደማይቀንስ ይልቁንም የተመጣጠነ የውሃ ፍሰት እንዲኖር በማድረግ የታችኞቹ ሀገራት ውሃው ለመስኖ እርሻ በአግባቡ መጠቀም እንደሚያስችል ብሎም ከደለል ነጻ የሆነ ውሃ ማግኘት እንደሚያስችላቸው በተደጋጋሚ ግልጽ ተደርጎላቸዋል።

ይሁን እንጂ በግብጽ በኩል “ታሪካዊ መብት” በሚል የቅኝ ዘመን ህግ እያጣቀሰች የግድቡ ግንባታ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ግድቡ ጥራት እንደሌለውና ሊደረመስ እንደሚችል በመግለጽ ከፍተኛ የፕሮፖጋንዳ ስራ በመስራት ውዥንብር ስትፈጥር ነበር፡፡ በአፍሪካ፣ በአውሮፓ፣ በሰሜን አሜሪካ፣ በእስያ እና በመካከለኛው ምስራቅ ግድቡን በመቃወም ከፍተኛ ዘመቻ አድርጋለች። የግድቡን ግንባታ የሚያከናውነው የሳሊኒ ኮንስትራክሽን ድርጅት ስራውን እንዲያቋርጥ በጣልያን መንግስትና በአውሮፓ ህብረት በኩል ከፍተኛ ጥረት አድርጋ አልተሳካላትም፡፡

ኢትዮጵያ የአባይን ውሃ ገድባ ልታስጠማን ነው የሚሉ መቀስቀሻዎች በሰፊው ስታካሄድ ቆይታለች። የሶስትዮሽ ዓለም አቀፍ የባለሙያዎች ቡድን ግብጽ፣ ኢትዮጵያ እና ሱዳን እያንዳንዳቸው ሁለት ባለሙያዎችን እንዲሁም 4 ዓለምአቀፍ ባለሙያዎች ከጀርመን፣ ከፈረንሳይ፣ ከደቡብ አፍሪካ እና ከእንግሊዝ ተቋቁሞ ባደረገው ጥናት ግድቡ በግብጽና ሱዳን ላይ ጉዳት እንደማያመጣ ይልቁን የተሻለ ጥቅምን እንደሚያስገኝ ይፋ አድርገዋል።

ከዚህ በተጨማሪ የግድቡ መጠን ከወንዙ ፍሰት ጋር የተመጣጠነ እንደሆነ፣ የግድቡ ዲዛይን እና ግንባታ ዓለምአቀፋዊ ደረጃን ያሟላል በማለት ገልጿል። የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት እውን እንዳይሆን ግብጽ ያልቆፈረችው ጉድጓድ የለም። ግብጽ ከያዘቻቸው ስትራቴጂዎች አንዱና ዋነኛው በኢትዮጵያ ውስጥ የተረጋጋ መንግስት እንዳይኖርና ሙሉ ትኩረቱን ፕሮጀክቱን ማስፈጸም ላይ እንዳያደርግ በውስጥና በውጭ የሚገኙ ያኮረፉ ሀይሎችን በመደገፍ አለመረጋጋት እንዲፈጠር ማድረግ ነው። ይህም በተለያዩ ጊዜያት የግብጽ መንግስታት በግልጽ ሲናገሩት የነበረ ሀቅ ነው።

አንዳንድ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ፕሮጀክቱ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት እንጂ ለልማት ታስቦ አይደለም እስከማለት የደረሰ ትችት ከማቅረብ አልፈው ‘ግድቡ ተሽጧል’ እስከማለት መድረሳቸው ይታወሳል።ግብጽ በህዳሴው ግድብ ውሃ አሞላል ዙሪያ ስታራምደው የቆየችው አቋም ሳይሳካላት ሲቀር የያዘችው አዲስ መከራከሪያ የውሃ ሙሌቱ እስከ 21 ዓመት በተራዘመ ጊዜ መሞላት አለበት የሚል ነበር። ይህም ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ በአመት 40 ቢሊዮን ሜትር ኪዮብ ውሃ እንድትለቅ እና የአስዋን ግድብ የውሃ መጠኑ ከምድር ወለል በላይ 165 ሜትር በላይ በማይሆንበት ወቅት ግድቡ ውሃ መያዝ እንደማይኖርበት ገልጻለች።

በተጨማሪም የታላቁ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት በሚገኝበት ቦታ አንድ ጽህፈት ቤት ተከፍቶ የግብጽና የሱዳን ተወካዮች የውሀውን የፍሰት መጠን እንዲቆጣጠሩም ጠይቃለች። ይህ የግብጽ አስተሳሰብ በሀገሪቱ ሉዓላዊ መብት ላይ የውጭ ሀይል በቀጥታ ጣልቃ እንዲገባ መፍቀድ በመሆኑ በኢትዮጵያ በኩል ተቀባይነትን አላገኘም።

ኢትዮጵያውያን በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ያሳዩት የአንድነት መንፈስ እጅግ ጠንካራ በመሆኑ የግድቡ ግንባታ ለአፍታም ቢሆን ሳይቆም ሥራው ቀጥሎ በሐምሌ 2012 ዓ.ም የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌት ማከናወን ችላለች። ይህ የውሃ ሙሌት ኢትዮጵያውያንን ያስፈነደቀ ሲሆን በአንፃሩ በግብጻውያን ዘንድ ድንጋጤ የፈጠረበት ክስተት ለመሆን በቅቷል።

ግብጽ ግድቡ እንዲስተጓጎል ያልፈነቀለችው ድንጋይ አልነበረም። ከአሜሪካ አደራዳሪነት እስከ የጸጥታው ምክር ቤትና የአረብ ሊግ ለማድረስ ብትሞክርም በሁሉም አቅጣጫዎች ያሰበችውን ማሳካት አልቻለችም። ባሳለፍነው 2012 ዓ.ም አሜሪካ የሶስትዮሽ ውይይቱን ከታዛቢነት ወደ አደራዳሪነት ብሎም የስምምነት ሰነድ አዘጋጅነትና አስገዳጅ ፊርማ ለማፈራረም ስትጀምር ኢትዮጵያ ራሷን አግልላለች።ይህን ተከትሎ የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የነበሩት ዶናልድ ትራምፕ ኢትዮጵያ በተዘጋጀው ሰነድ ላይ የማትፈርም ከሆነ ግብጽ የህዳሴው ግድብ ልታፈነዳው ትችላለች’ በማለት ማስፈራሪያ አዘል መልእክት አስተላልፈዋል።

በተጨማሪም ለኢትዮጵያ ሊሰጥ የነበረውን የገንዘብ ድጋፍ እንዲታገድ አድርገዋል። ኢትዮጵያ ይህን ሁሉ ጫና በመቋቋም ድርድሩ ወደ አፍሪካ ህብረት እንዲመጣ አድርጋለች። ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት በብዙ ተግዳሮቶች ያለፈ እንደመሆኑ ይጠናቀቃል ተብሎ በተያዘለት የአምስት ዓመታት የጊዜ ገደብ ማጠናቀቅ አለመቻሉ በህዝቡ ዘንድ ቅሬታን መፍጠሩ አልቀረም።

ይህም ተጨማሪ ወጪን የጠየቀ ከመሆኑ ባሻገር በህብረተሰቡ ዘንድ ጥርጣሬ እንዲፈጠር ያደረገ ክስተት ነበር። የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ስራ አስኪያጅ መሀንዲስ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ ከዓመት በፊት ለመገናኛ ብዙሀን በሰጡት ማብራሪያ ፕሮጀክቱ በተያዘለት በጀት፣ በታቀደለት ጊዜና በሚጠበቀው ጥራት እንዳይጠናቀቅ ካደረጉት ምክንያቶች መካከል ከግብጽና ሱዳን እንዲሁም ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጫና በበለጠ የፕሮጀክቱን የኤሌክትሮ ሜካኒካል ዘርፉ ዕውቀትና ልምድ ላልነበረው ለሜቴክ እንዲሰጥ በመደረጉ ነው ሲሉ ገልጸው እንደነበር የሚታወስ ነው።

አዲሱ የለውጥ አመራር ወደ ስልጣን መምጣቱን ተከትሎ በፕሮጀክቱ ዙሪያ በተደረገ ጥልቅ ግምገማ ግድቡ በበርካታ ችግሮች መተብተቡና አፈጻጸሙም ከሚጠበቀው በታች መሆኑን በግልጽ ተለይቷል። በዚህም የኤሌክትሮ ሜካኒካል ዘርፉ በአፈጻጸም ፍጥነትም ሆነ ጥራት ላይ ከፍተኛ ጉድለት የነበረበት መሆኑን ታውቋል። ፕሮጀክቱ ለአጠቃላይ ሀገራዊ ልማት ያለውን አንድምታ ግምት ውስጥ በማስገባት ሜቴክ ይዞት የነበረውን የፕሮጀክቱን ክፍል በዘርፉ ከፍተኛ እውቀትና ልምድ ላላቸው የውጭ እና የሀገር ውስጥ ተቋራጮች በመስጠት ስራው በሚፈለገው ጥራትና ፍጥነት እንዲጠናቀቅ ባሳለፈው ውሳኔ መሰረት አሁን አጠቃላይ ስራውን ለማጠናቀቅ ከ20 በመቶ ያልበለጠ ደረጃ ላይ ደርሷል።

የግድቡ ግንባታ መጓተት ሀገሪቱ በየዓመቱ የአንድ ቢሊዮን ዶላር ተጨማሪ ወጪ እንድታወጣ እንዳደረገ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ በቅርቡ ለተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሰጡት ማብራሪያ ጠቅሰዋል፡፡ የግድቡ ፕሮጀክት ግንባታ ከተጀመረ እነሆ 10ኛ ዓመቱን ደፍኗል፡፡

በዚህ ሂደት ፕሮጀክቱ ቀላል የማይባል ተግዳሮቶች ውስጥ አልፏል።ይህም ሆኖ በህዝቡ ያልተቋረጠ ድጋፍ ሥራው እንዲቀጥል ተደርጎ የመጀመሪያው ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት ተከናውኗል። ዘንድሮ ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት ለማከናወን ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል። የሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌቱ ግብጽን እና ሱዳንን አንገብግቧቸዋል። በሙሌቱና በኦፕሬሽኑ ዙሪያ አስገዳጅ ህግ ካልተፈራረምንና ያለእኛ ይሁንታ ጠብታ ውሃ እንዳትነኩ በማለት መዛት ጀምረዋል።

ስለሆነም የመሰረት ድንጋይ የተጣለበት 10ኛ ዓመት ሲከበር ሀብት የማሰባሰብ ስራው ተጠናክሮ እንዲቀጥል ማድረግ ያስፈልጋል። ለግድቡ እውን መሆን ከጅምሩ አንስቶ የበኩሉን አዎንታዊ ሚና ያልተጫወተ ኢትዮጵያዊ የለም፡፡ ሊጠናቀቅ ከጫፍ የደረሰውንና የግንባታ ሂደቱ 79 በመቶ የደረሰውን የህዳሴ ግድብ ቀሪ ሥራዎች ለማጠናቀቅ አሁንም የሁሉም ኢትዮጵያውያን የተቀናጀ ርብርብ ያስፈልጋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም