በደብረ ማርቆስ ዙሪያ 3 ሺህ ሜትር የኤሌክትሪክ ገመድ በመሰረቅ ወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ

65

ደብረ ማርቆስ ፤ መጋቢት 24/2013 (ኢዜአ) በደብረ ማርቆስ ዙሪያ አካባቢው 3 ሺህ ሜትር ርዝመት ያለው የኤሌክትሪክ መስመር የተዘረጋበት ገመድ በመስረቅ ወንጀል የተጠረጠሩ አራት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ማዋሉን ፖሊስ አስታወቀ።

የደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ዋና ኢንስፔክተር አጃናው አዲስ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ የኤሌክትሪክ ገመዱ የማስተላለፊያ ምሶሶን  በመቁረጥ  መጋቢት 22/2013 ዓ.ም. ምሽት ተሰርቋል።

ፖሊስ ባደረገው ጥብቅ ክትትል የኤሌክትሪክ ገመዱ በደብረ ማርቆስ ከተማ  ቀበሌ አንድ ግለሰብ ቤት ተደብቆ መገኘቱን አመልክተዋል።

በጉዳዩ የተጠረጠሩ አራት ግለሰቦች ተይዘው ፖሊስ ምርመራ እያደረገ መሆኑን የገለጹት ዋና ኢንስፔክተሩ ፤ሌሎችም ግብረ አበሮች እንዳሉ በመጠርጠሩ ለመቆጣጠር በክትትል ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የደብረ ማርቆስ ኤሌክትሪክ ሃይል መካከለኛ መስመር ሃላፊ አቶ ባንቲሁን ደመላሽ በበኩላቸው የግል ጥቅም  በሚፈልጉ ግለሰቦች የኤሌክትሪክ መስመር ዝርፊያ በተደጋጋሚ እየተፈፀመ መሆኑን ተናግረዋል።

ከትናንት በስቲያ  በደብረ ማርቆስ ዙሪያ   የተዘረጋውን የኤሌክትሪክ ገመድ የተሸከሙ አስር ምሶሶዎችን   በመቁረጥ ከ3ሺህ ሜትር በላይ ገመድ ተዘርፏል ብለዋል።

በወንጀሉ የተጠረጠሩ በፖሊስ መያዛቸውንና የኤሌክትሪክ ሃይል መስሪያ ቤቱም መልሶ በመጠገን ዛሬ እኩል ቀን አገልግሎት እንዲሰጥ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።

በዚህም የሃይል አቅርቦት ተቋርጦባቸው የነበሩ ደንበጫ፣ ፍኖተሰላም፣ ሽንዲ፣ ቁጭ፣ ዋድ፣ የዘለቃ፣ በከፍል ፈረስ ቤት እንዲሁም ማንኩሳ ከተሞች መልሰው አገልግሎቱን እንዲያገኙ ተደርጓል ብለዋል።

በዚህ ዝርፊያም ከ600 ሺህ ብር በላይ ኪሳራ መድረሱን ጠቁመው ፤ በደብረ ማርቆስ ከተማ ቀደም ሲልም እስከ 5 ሚሊዮን ብር የሚገመት  36 ሺህ 200 ሜትር የኤሌክትሪክ  ገመድ መሰረቁን አስታውሰዋል።

መንግስት መሰረተ ልማትን መዘርጋት ግዴታው ቢሆንም የተዘረጋውን መስመር በባለቤትነት ህብረተሰቡ መጠበቅ እንዳለበትም አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም