ምክትል ከንቲባ አዳነች ከቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ - ጎሮ የ4 ነጥብ 9 ኪሎ-ሜትር የአስፓልት መንገድ ግንባታን አስጀመሩ

78

አዲስ አበባ መጋቢት 24/2013 /ኢዜአ/የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ - ጎሮ የሚገነባውን 4 ነጥብ 9 ኪሎ ሜትር የአስፓልት መንገድ አስጀመሩ፡፡

መንገዱ በ1 ነጥብ 6 ቢለየን ብር ወጪ የሚገነባ ሲሆን ሙሉ ወጪውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር ይሸፍናል፡፡

በግንባታ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት ምክትል ከንቲባዋ አስተዳደሩ የከተማዋን የመንገድ ፍላጎት ለማሟላት በትኩረት እየሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡ 


አሁን ያለው የመንገድ ሽፍን ከከተማዋ እድገት ጋር የማይመጣጠን መሆኑን ገልጸው ለማስፋፋትና ጥራቱን የጠበቀ መንገድን ለማዳረስ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡ 


አሁን ያለው የከተማዋ የመንገድ ሽፋን ከ20 በመቶ እንደማይበልጥም በመጠቆም፡፡

በከተማዋ ፕሮጀክቶችን በተያዘላቸው የጊዜ ገደብና በፍጥነት ማጠናቀቅ ባህል ሆኗል ያሉት ከንቲባዋ አሁንም ለህዝቡ የመሰረተ ልማቶችን ለማሟላት ፍጥነት ወሣኝ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ዛሬ ግንባታው የተጀመረው የቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ - ጎሮ ፕሮጀክትም በተያዘለት የጊዜ ገደብ ለማጠናቀቅ ቀን ከሌት መሰራት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡


የአከባቢው ማህበረሰብም ለመንገዱ ግንባታ መፋጠን የሚጠበቅባቸውን ሁሉ አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡

የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ሞገስ ጥበቡ በበኩላቸው ከቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ - ጎሮ የሚገነባውን 4 ነጥብ 9 ኪሎ-ሜትር ርዝመት ያለው መሆኑን ገልጸዋል፡፡


ለመንገዱ ግንባታም የ24 ወራት የጊዜ ገደብ የተያዘ መሆኑን የገለጹት ኢንጅነሩ በ60 ሜትር የጎን ስፋት እንደሚገነባም ጠቁመዋል፡፡


የመንገዱን ግንባታ የሚያከናውነው አሰር የተባለው ኮንስትራክሽን ሲሆን የማማከር ስራውን ደግሞ ዩኒኮን የተባለ አማካሪ ድርጅት እንደሚከታተለው ተናግረዋል፡፡


የመንገድ ፕሮጀክቱ ግንባታ በ1 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር ወጪ ይገነባል።


ከቦሌ ኢንተርናሽናል ኤርፖርት ቪአይፒ ተርሚናል እስከ ቦሌ ሆምስ ድረስ ያለው 1 ነጥን 5 ኪሎ-ሜትር በሁለት ወራት ውሰጥ ተጠናቆ ከቦሌ ቪአይፒ ተርሚናል ጋር አብሮ የሚመረቅ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡


የመንገድ ፕሮጀክቱ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅም   የትራፊክ ፍሰትን  ያሳልጣል ብለዋል፡፡ 


በከተማዋ ከ100 በላይ የመንገድ ፕሮጀክት እየተገነቡ መሆናቸውን የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ኢንጅነር ሞገስ ገልጸዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም