በህዳሴ ግድቡ ሰበብ በኢትዮጵያ ለይ የሚደርሰው ጫና የአገሪቱን ተሰሚነት ባለመፈለግ መሆኑን ምሁራንና ፖለቲከኞ

76

አዲስ አበባ መጋቢት 24/2013 /ኢዜአ/ የህዳሴ ግድብን በተመለከተ በኢትዮጵያ ላይ ከአንዳንድ አገራት እየደረሰ ያለው ጫና የአገሪቱን ተሰሚነትና እድገት ካለመፈለግ የመጣ መሆኑን ምሁራንና ፖለቲከኞች ተናገሩ።

የህዳሴው ግድብና አለም አቀፍ ጉዳዮችን በተመለከተ በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ የዲፕሎማሲና አለም አቀፍ መምህርና የትምህርት ክፍሉ ሃላፊ አቶ እንዳለ ንጉሴና በአዲስ አበባ የኢዜማ እጩ አባል አቶ ሃብታሙ ኪታባ ለኢዜአ ሃሳባቸውን አካፍለዋል።

ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ የምትከተለው ዲፕሎማሲያዊ አካሄድ ሁሉን አቀፍ ፣በወዳጅነትና አብሮ መስራት ላይ ያተኮረ መሆኑ ተናግረዋል።

የአባይ ወንዝ 86 በመቶ ምንጭ የሆነችው ኢትዮጵያ የውሃው ተጠቃሚ ሳትሆን እስካሁንም ዘልቃለች።

ኢትዮጵያ የአባይን ወንዝ ለመጠቀም በተለያየ ዘመን ብዙ ብትሞክርም በተለይ በግብፅ በኩል የሚደረጉ አለማቀፋዊ ጫናዎች፣ ውስጣዊ ክፍፍልና አለመስማማት የመፍጠር አዝማሚያዎች ተደምረው ሳይሳኩላት ቀርተዋል፡፡

ኢትዮጵያ በራሷ ሉዓላዊ ግዛትና በራሷ ወንዝ ላይ የሚገነባ አንድ ትልቅ ግድብ የታችኞቹን ሃገራት ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ ግልፅ አሰራር ማዘጋጀቷ የመጀመሪያዋ ሃገር የሚያደርጋትና የሚያስመሰግናት መሆኑንም አንስተዋል።

ይሁን እንጂ በተለይ የህዳሴው ግድብ ወደ መጠናቀቅ ሲመጣ የኢትዮጵያን ከፍታና እድገት የማይፈልጉ ሃገራት በኢትዮጵያ ላይ ጫና እያሳደሩ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ጫናው አንድም የራሳቸውን ብሄራዊ ጥቅም ከማስጠበቅ በሌላ በኩል ደግሞ የኢትዮጵያ መፃኢ እድገትና ተሰሚነት የማይፈልጉ መሆናቸውን የሚያሳይ እንጂ ከህዳሴው ግድብ ግንባታና ከውሃ አጠቃቀም ኢፍትሃዊነት ጋር የተያያዘ እንዳልሆነ አንስተዋል።

በተለይም በኢትዮጵያ የታየው የፖለቲካዊ ለውጥ ፣ የግድቡ መሞላት፣የውጭ ጉዳይ ፖሊሲው ወደ ዜጋ ተኮር መቀየርና እየታዩ ያሉት የእድገት አመላካቾች ይህን ለውጥ ለማይፈልጉ የውስጥና የውጭ አካላት ራስ ምታት መሆኑንም ይገልፃሉ።

ይህም ኢትዮጵያ የአባይን ወንዝ እንዳትጠቀም የሚያደርጉትን አለማቀፋዊ ጫናና ህዝቦቿን የመከፋፈል የፖለቲካ ሴራ በተለያየ መንገድ እንዲያጠናክሩ አድርጓቸዋል ብለዋል።

የህዳሴው ግድብ ለኢትዮጵያዊያን የአንድነት መሰረትን የሚያጠናክር፣ የኢኮኖሚ እድገትን የሚያፋጥንና የሀገሪቱን አለም አቀፍ ተሰሚነት የሚያጎላ መሆኑን ተናግረዋል።

የተለያዩ አለም አቀፍ ተቋማትና ሃገራት እንዲሁም በጥቅም የሚገዙ ምሁራን በቂ ማስረጃ ሳይዙ በተለያዬ መንገድ ጫና ሲያደርጉ እንደሚታዩም አቶ እንዳለ ጨምረው ገልፀዋል ።

በተለይ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲና ዲፕሎማሲው ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ እንዲሆን መደረጉ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በጋራ ስለ ሃገሩ ሉአላዊነት እንዲሰራ መልካም አጋጣሚን መፍጠሩም ተጠቅሷል።

እንደዚህ አይነት ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮችን ማሸነፍ የሚቻለው በጋራ ለሃገር ጥቅም በመቆም ሲቻል መሆኑንም አቶ እንዳለ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም