በመጋቢት ወር ብቻ ከ4 በላይ ብሔራዊ ፓርኮች እና ጥብቅ ደኖች ላይ የእሳት አደጋ ተከስቷል

116

  አዲስ አበባ መጋቢት 24/2013 /ኢዜአ/ በኢትዮጵያ በዘንድሮው መጋቢት ወር ብቻ ከ4 በላይ በሚሆኑ የተለያዩ ብሔራዊ ፓርኮች እና ጥብቅ ደኖች ላይ የእሳት አደጋ መከሰቱን የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን አስተወቀ።

በተደጋጋሚ በፓርኮቹ ላይ የሚደርሰውን የእሳት አደጋ በዘላቂነት ለመፍታትም በሁሉም ብሔራዊ ፓርኮች ላይ “የእሳት መከላከል ብርጌድ” ተቋቁሞ ወደ ስራ መገባቱ ተገልጿል።

ኢትዮጵያ ባሏት በርካታ ታሪካዊ፣ ተፈጥሯዊና ባህላዊ ቅርሶችና ሃብቶቿ ከአፍሪካ ቀዳሚ እንደሆነች ይነገራል።

የቱሪስት መስህብ የሆኑ የተፈጥሮ ሃብቶች እና ብሔራዊ ፓርኮች፣ ብርቅዬ የዱር እንስሳት፣ አእዋፋትና እጽዋት ያሉባት አገር መሆኗም ተመራጭ ያደርጋታል። 

የዱር እንስሳትን እና መኖሪያቸውን በመጠበቅና በማልማት ዘላቂ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ ይታመናል።

ይሁንና እነዚህ ሃብቶቿ በተለያዩ ምክንያቶች አደጋዎች ላይ በየጊዜው እየወደቁ መሆናቸው ይስተዋላል።

ከቅርብ ጊዜያቶች ወዲህ በአገሪቱ በሚገኙ የተለያዩ ብሔራዊ ፓርኮች ላይ የሰደድ እሳት አደጋ ደርሶ ውድመት አስከትሏል።

ለመሆኑ የእነዚህ በተደጋጋሚ እያጋጠሙ ያሉ አደጋዎች መንስኤዎች እና ዘላቂ መፍትሄዎቻቸው ምን ይሆን?

የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን መኮንን ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በተያዘው መጋቢት ወር ብቻ በአማራ፣ ኦሮሚያ፣ አፋርና ደቡብ ክልሎች ከአራት በላይ የሚሆኑ ብሔራዊ ፓርኮች ላይ የእሳት አደጋ ተከስቷል።

አላይ ዴጌ አሰቦት እጩ ብሔራዊ ፓርክ፣ ሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ፣ ባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ እንዲሁም አማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ጣርማ በር ወፍ ዋሻ ላይ ተመሳሳይ አደጋዎች መከሰታቸውን ገልጸዋል።

በየአመቱ እየተከሰቱ ያሉ የሰደድ እሳት አደጋዎች በተፈጥሮ ሃብቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሱ ይገኛሉ።

ከሰሞኑ በፓርኮቹ ላይ የደረሰው አደጋም እድሜ ጠገብ የሆኑ ደኖች እንዲወድሙ እና እንስሳቱም እንዲሞቱ ማድረጉን አቶ ሰለሞን ተናግረዋል።

በአብዛኛው በፓርኮች ላይ የሚደርሱ የሰደድ እሳት አደጋዎች ሰው ሰራሽ ሲሆኑ ከህገ-ወጥ ሰፈራ፣ እርሻ፣ ደን ጭፍጨፋ፣ አደንና ከሰል ማክሰል ጋር በተያያዘ የሚከሰቱ ናቸው።

ከሰሞኑ በፓርኮቹ ላይ የተከሰቱት የሰደድ እሳት አደጋዎችም ከእነዚሁ ችግሮች ጋር ተያይዞው የመጡ መሆናቸውንም አብራርተዋል።

ይሁንና እነዚህን አደጋዎች የፖለቲካ አጀንዳ በማስመሰል የሚናፈሱ ወሬዎች ያሉ ሲሆን አደጋዎቹ ምንም አይነት ከፖለቲካ ጋር የሚያያዝ ምክንያት የሌላቸው መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

በፓርኮቹ ላይ በተደጋጋሚ ጊዜ እየደረሱ የሚገኙ አደጋዎችን ለመቀነስ እሳቱ ከተፈጠረ በኋላ ለመቆጣጠር ብቻ ሳይሆን ከመከሰቱ በፊት የቅድመ መከላከል ስራ የሚሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም ህብረተሰቡ ግንዛቤ እንዲኖረው ከማድረግ ባሻገር በፓርኮቹ እና መጠለያ ጣቢያዎች ላይ ሆን ብሎ አደጋው እንዲፈጠር ምክንያት የሚሆኑ አካላት ለህግ እንዲቀርቡ እና ተጠያቂ እንዲሆኑ የማድረግ ስራ የሚጠናከር መሆኑንም ተናግረዋል።

በፓርኮቹ ላይ በደረሰው አደጋ የወደመው ሃብት በቀጣይም በጥናት ተደግፎ የሚገለጽ መሆኑን ጠቁመዋል። 

በቀጣይም ይበልጥ ለእሳት አደጋው መከሰት ሊጋለጡ የሚችሉ ፓርኮችን በመለየት ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር የጋራ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ ብለዋል።

በሁሉም ብሔራዊ ፓርኮች  “የእሳት መከላከል ብርጌድ” ተቋቁሞ ወደ ስራ መገባቱን ገልጸዋል።

በሌላ በኩልም ለችግሩ ዘላዊ መፍትሄ ለማበጀት የእሳት ማጥፊያ ሔሊኮፕተሮች እንዲኖሩ ለማስቻል መንግስት ድጋፍ እንዲያደርግ መጠየቁን ተናግረዋል።

ህብረተሰቡ በእኔነት ስሜት ሃብቶችን በመጠበቅ ለትውልድም እንዲተላለፍ ለማድረግ መስራት እንደሚገባው አሳስበዋል።

በኢትዮጵያ በአጠቃላይ 27 የሚሆኑ ብሔራዊ ፓርኮች እንደሚገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም