በዞኖቹ በክረምት የሚተከሉ 434 ሚሊየን ችግኞች እየተዘጋጁ ነው

116

ምስራቅ ጎጃም/ ወልዲያ መጋቢት 23/2013 (ኢዜአ) በምስራቅ ጎጃምና ሰሜን ወሎ ዞኖች በመጭው ክረምት በመደበኛውና በአረጓዴ አሻራ መርሀግበር የሚተከሉ 434 ሚሊየን ችግኞች እየተዘጋጁ መሆኑን የየዞኖቹ ግብርና መምሪያዎች አስታወቁ።

የምራቅ ጎጃም ዞን ግብርና መምሪያ የተፈጥሮ ሀብት የስራ ሂደት ቡድን መሪ አቶ ንጉሴ ሽመልስ ለኢዜአ እንደገለጹት በመጭው ክረምት በመደበኛና በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የሚተከሉ 242 ሚሊየን ችግኞች እየተዘጋጁ ነው።

ችግኞቹ እየተዘጋጁ ያሉት  በ230 የመንግስት፣ የግለሰቦችና የማህበራት ጣቢያዎች ነው።

እየተዘጋጁ ያሉት ችግኞች ዋንዛ፣ ግራቭሊያ፣ ዲከረንስ፣ ወይራ፣ ብሳና፣ ጽድና ሌሎች ሀገር በቀልና የውጭ ዝርያ ያላቸው የዛፍ አይነቶች ናቸው።

ችግኞቹ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለቸው መሆናቸውን የገለጹት ቡድን መሪው በደን ክልል ጨምሮ በግልና በወል መሬቶች ላይ እንደሚተከሉ አመላክተዋል።

የጎዛምን ወረዳ የጥጃን ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ሰላም ሰው ታረቀኝ በሰጡት አስተያየት በየዓመቱ ሀገር በቀል ዝርያ ያላቸው የዋንዛና ወይራ ችግኞችን እያፈሉ ለገበያ እያቀረቡ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በመጭው ክረምት በግላቸው የሚተክሉትና ለሽያጭ የሚያቀርቡትን ችግኝ እያዘጋጁ እንደሆነ አስታውቀዋል።

በዞኑ ባለፈው አመት  በመደበኛውና በአረጓዴ አሻራ መረሃ ግብር ከተተከሉ 241ሚሊየን የሚሆኑ ችግኞች ውስጥ 82 በመቶ መጽደቃቸውን የዞኑ ግብርና መምሪያ መረጃ አመላክቷል።

በተመሳሳይ በሰሜን ወሎ ዞን በመጭው ክረምት የሚተከሉ 192 ሚሊዮን  ችግኞች እየተዘጋጁ መሆኑን  የዞኑ ግብርና መምሪያ ምክትል ሃላፊ አቶ ተገኘ አባተ አስታውቀዋል።

እየተዘጋጁ ያሉት ችግኞች ወይራ፣ የአበሻ ጥድ፣ ዋንዛ፣ ኮሶ፣የባህር ዛፍና ሌሎች የሀገር በቀልና  የውጭ ዝርያ ያላቸው የዛፍ አይነቶች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

የችግኝ ዝግጅቱ በመንግስት ሞዴል ጣቢያዎች እንዲሁም  በማህበራትና በአርሶ አደሮች ማሳ እየተካሄደ መሆኑን አመልክተዋል።

እየተዘጋጁ ካሉት ችግኞች ውስጥ 22 ሚሊዮን የሚሆኑት  በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በአንድ ቀን የሚተከሉ መሆኑን ተናግረዋል።

"ቀሪዎቹ ደግሞ በመደበኛው መርሀ ግብር የተከላሉ" ብለዋል።

ተከላው ከሚካሄድባቸው ስፍራዎች ውስጥ እስካሁን 12 ሺህ 261 ሄክታር መሬት ተለይቶ ካርታ እንደተዘጋጀለት የመምሪያው ምክትል ሀላፊ አስታውቀዋል።

በመቄት ወረዳ የቀበሌ 08 ነዋሪ አርሶ አደር ተመስገን ውቡ በመጭው ክረምት በግላቸው የሚተክሉትን 4ሺህ የባህር ዛፍ ችግኝ ማዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

በዞኑ ባለፈው ዓመት የተተከሉና የጸደቁ 139 ሚሊዮን ችግኞች ማህበረሰቡ እንክብካቤና ጥበቃ እየተደረገላቸው መሆኑን የዞኑ ግብርና መምርያ መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም