በጉጂና ባሌ ዞኖች ለ525 ሺህ በላይ ህጻናት የልጅነት ልምሻ መከላከያ ክትባት ተሰጠ

75

ነገሌ/ጎባ ፤ መጋቢት 23/2013(ኢዜአ) በጉጂ እና ባሌ ዞኖች ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች ለሆኑ ከ525 ሺህ ለሚበልጡ ህጻናት የልጅነት ልምሻ /ፖሊዮ/ መከላከያ ክትባት በዘመቻ መሰጠቱ ተገለጸ።

ቤት ለቤት ከተሰጠው ክትባት ውስጥ  በጉጂ ዞን 316 ሺህ ህጻናትን በማዳረስ የተከናወነው ከፍተኛውን ቁጥር የያዘ ነው።

በዞኑ ጤና ጽህፈት ቤት  የክትባት መርሃ ግብር አስተባባሪ አቶ መስፈን ካሳዬ እንደተናገሩት፤ ክትባቱ የተሰጠው በጉጂ  16 ወረዳዎች  ከ3 ሺህ 300 የሚበልጡ የጤና ባለሙያዎችና ድጋፍ ሰጪዎችን በማሳተፍ ነው፡፡ 

የጸጥታ ስጋት ካለባቸው ሁለት ወረዳዎች በስተቀር በዘመቻው በተሰጠው ክትባት ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ህጻናት ማዳረስ መቻሉን አስረድተዋል፡፡

በተመሳሳይ በባሌ ዞን  ለ209 ሺህ ህጻናት ቤት ለቤት  ክትባቱ መሰጠቱን የዞኑ ጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት  ምክትል ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ቱጁባ ለኢዜአ ገልጸዋል።

ክትባቱ የተሰጠው ከመጋቢት 17 /2013 ዓ.ም ጀምሮ  ለአራት ቀናት  በ12 የዞኑ ወረዳዎች በየደረጃው የሚገኙ የጤና ባለሙያዎች፣ ተቆጣጣሪዎችና መንገድ መሪዎች በማሳተፍ መሆኑን ተናግረዋል።


እንደ ምክትል ኃላፊው ገለጻ፤ ከጎረቤት ሀገራት ወደ ሀገር ውስጥ በድንበር አካባቢ ሊገባ የሚችለውን የልጅነት ልምሻ በሽታ አስቀድሞ ለመከላከል ክትባቱ ተሰጥቷል፡፡

በዘመቻ ከተሰጠው ክትባት በበተጓዳኝ  በዞኑ የኮሮና  ወረርሽኝ ለመከላከል  የህብረተሰቡን ግንዛቤ የማጠናከር ስራ መከናወኑንም ተናግረዋል።


ለፖሊዮ መከላከያ ክትባቱ ዘመቻ ውጤታማነት የጤና ሚኒስቴር፣ የኦሮሚያ ጤና ቢሮና የህጻናት አድን ድርጅት/ዩኒሴፍን  ጨምሮ ሌሎች መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ድጋፍ ማድረጋቸው ተመልክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም