ሴቶች ወደ አመራርነት መምጣታቸው ለመጪው ትውልድ ተስፋ የሚሰጥ መሆኑ ተገለጸ

180

  አዲስ አበባ መጋቢት 22/2013 (አዜአ)በርካታ ሴቶች ወደ አመራር ሰጪነት መምጣታቸው ለመጪው ትውልድ ተስፋን የሚሰጥና ተነሳሽነትን የሚፈጥር እንደሆነ ተገለጸ።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሴቶች የልህቀት ቀንን የዩኒቨርሲቲው የስራ ሃላፊዎችና ሴት ተማሪዎች በተገኙበት አክብሯል።

በዕለቱም በትምህርት ዘርፍ በጎ ተጽእኖ ማሳረፍ የቻሉ ሴት ምሁራን የህይወት ተሞክሯቸውን አጋርተዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ዳይሬክተር ወይዘሮ ማተቤ ታረቀኝ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፣ ተጽእኖ ፈጣሪ ሴቶች የህይወት ተሞክሯቸውን ማጋራታቸው ለተተኪው ትውልድ መነቃቃትን የሚፈጥር ነው።

አሁን ላይ ሴቶች በብዛት ወደ አመራርነት እየመጡ እንደሆነና ባልተለመደ መልኩ የዩኒቨርሲቲው ሁለት ምክትል ፕሬዝዳንቶች ሴቶች መሆናቸውን ገልጸዋል።

''ይህም ሴቶች ከዚህ ቀደም ከነበረው በተሻለ ሁኔታ ወደ አመራር ሰጪነት እየመጡ መሆኑን ማሳያ ነው'' ብለዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህክምና ሳይንስ ኮሌጅ የውስጥ ደዌ መምህር ፕሮፌሰር የወይንሐረግ ፈለቀ  ''የሴቶች የህይወት ጉዞ ውስብስብና ጽናትን የሚጠይቅ ነው ብለዋል''።  

በዚህም ሴቶች በቁርጠኝነት ከሰሩ በተሰማሩበት የስራ መሰክና የአመራር ሰጪነት ቦታ ተግባራቸውን በብቃት መወጣት እንደሚችሉ ማየት ተችሏል ብለዋል።

''ሁሉም ነገር የሚጀምረው በቅድሚያ ራስን ከመቀበል ነው ''ያሉት ፕሮፌሰሯ ራሱን የተቀበለና በራሱ የሚተማመን ትውልድ በእንችላለን መንፈስ ሁሉን ማድረግ ይችላል ብለዋል።

በእለቱ የተገኙት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሴት ተማሪዎችም የቀረቡት የህይወት ተሞክሮዎች ተነሳሽነትንና ተስፋን እንደፈጠረላቸው ገልጸዋል።

በጀመሩት የትምህርትና የህይወት ጉዞ ውስጥ የሚያጋጥሟቸውን ተግዳሮቶች በጽናት ለማለፍ መሰል ተሞክሮዎች አስፈላጊ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የሴቶች የልህቀት ቀን ዘንድሮ ለ10ኛ ጊዜ ተከብሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም