የሃሰተኛ መረጃ ስርጭት በምርጫው ሰላማዊ ሂደት ላይ ተጽእኖ እንዳያሳድር የመረጃ ትክክለኝነት ማጣሪያ ስርዓት ሊዘረጋ ይገባል ተባለ

82

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 22 /2013 (ኢዜአ) የሃሰተኛ መረጃ ስርጭት በምርጫው ሰላማዊ ሂደት ላይ ተጽእኖ እንዳያሳድር የመረጃ ትክክለኝነት ማጣሪያ ስርዓት ሊዘረጋ እንደሚገባ ተጠቆመ።

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የሚዘጋጀው የአዲስ ወግ የውይይት መድረክ "ሃሰተኛ መረጃ በሰላማዊ ምርጫ ላይ ያለውን አሉታዊ ተጽእኖ እንዴት መግታት ይቻላል?" በሚል ርዕስ ውይይት ተካሂዷል።

በውይይቱ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት ኃላፊዎችን ጨምሮ ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

የመገናኛ ብዙኃን የሕግ ማሻሻያ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ሰለሞን ጎሹ እና ጋዜጠኛ ኤደን ብርሃኔ የመወያያ መነሻ ሃሳብ አቅርበዋል።

አቶ ሰለሞን በዚሁ ወቅት በኢትዮጵያ ያለው የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ቁጥር በፍጥነት እያደገ መሆኑን ጥናቶች እንደሚያሳዩ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ያለው የፖለቲካ ሽግግር የሰከነ አለመሆን እና የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ግንዛቤ አለመጎልበት ደግሞ በኢትዮጵያ ያሉ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎችን ለሃሰተኛ መረጃ ተጋላጭ እንዲሆኑ ማድረጉን አንስተዋል።

በተለይ ከምርጫው ጋር በተያያዘ ማንነታቸው ያልታወቁ ግለሰቦች በተደራጀ መልኩ በሃሰተኛ መረጃ ስርጭት ላይ እንዲሳተፉ እድል እንደሚከፍትም ገልጸዋል።

ለዚህ ደግሞ ከወዲሁ ምልክቶች እየታዩ ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ የህግ ማእቀፍን በመጠቀም የሀሰተኛ መረጃና የጥላቻ ንግግርን ለመቆጣጠር ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ነገር ግን ችግሩን ለመቅረፍ ከህግ አሰራር በተጨማሪ ሃቅ ማጣራት እና ስለ ጉዳዩ ተከታታይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች መከናወን እንዳለበት ተናግረዋል።

የበርካታ አገራት ልምድ ይህን እንደሚያሳይ በመጠቆም።

ጋዜጠኛ ኤደን ብርሃኔ በበኩሏ ምርጫ የብዙ ሰዎች ፍላጎትና ትኩረት የሚይዝ በመሆኑ የሃሰተኛ መረጃዎች ስርጭት እንዲጨምር እንደሚያደርግ ገልጻለች።

ችግሩን ለመቅረፍ ደግሞ የተጠናከረ የሃቅ ማጣራት ስርዓት ሊዘረጋ ይገባል ብላለች።

የሃቅ ማጣራት ስርዓት ከማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች በተጨማሪ ሌሎች መንግስታዊ አካላት የተሳሳተ ውሳኔ እንዳይወስኑ እንደሚያደርግም ነው የተናገረችው።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ዜጎች ለሃሰተኛ መረጃ ተጋላጭ እንዳይሆኑ በተለይ የመረጃ ተደራሽነት ላይ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

በተጨማሪ መደበኛ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ፈጣን መረጃን ከማድረስ ጎን ለጎን ሃቅ ማጣራት ላይ የሚሰራ የተደራጀ ክፍል መቋቋም እንዳለባቸውም ሃሳብ አንስተዋል።

ይህን ለማድረግ ደግሞ መደበኛ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ያሉባቸው የበጀት እጥረቶች ሊቀረፉላቸው ይገባል ነው ያሉት

ከምርጫው ባለፈ ጤናማ መረጃ ፍሰትን በዘላቂነት እንዲኖር የሃቅ ማጣራት ስርዓትን በቀጣይነት ገቢራዊ መሆን እንዳለበትም አንስተዋል።

የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችም ህጋዊ የሆነ የማህበራዊ ሚዲያ አካውንት ከፍተው መጠቀም እንዳለባቸውም ተሳታፊዎቹ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ለ6ኛ ጊዜ ለሚካሄደው የዘንድሮው አጠቃላይ ምርጫ የመራጮች ምዝገባ በመካሄድ ላይ መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም