ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ቦንድ በመግዛት ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ በባሌ ዞን ነዋሪዎች ገለጹ

121

መጋቢት 22/2013 (ኢዜአ)  ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ቀሪ ስራን ለማጠናቀቅ ቦንድ በመግዛት የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ በባሌ ዞን አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡

በዞኑ ባለፉት ሁለት ሳምንታት በተካሄደው የቦንድ ሽያጭ ሳምንት  ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መገኘቱን የዞኑ የህዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት አስታውቀዋል፡፡

በባሌ ዞን  ሲናና ወረዳ የወቾ ቀበሌ ነዋሪ ወጣት አህመድ ከድር እንዳለው፤ ታላቁ የኢትዮጵያ  ህዳሴ ግድብ ግንባታ ለወጣቶች የወደፊት ተስፋ ነው።

የግድቡ ግንባታ ከውስብስብ ችግር ተላቆ የመጀመሪያ ዙር ውሃ ሙሌት መጠናቀቅ በፈጠረብኝ መነሳሳት የ2 ሺህ ብር ቦንድ ግዥ ፈጽሚያለሁ ብሏል።

በተሰማራበት አነስተኛ የንግድ ስራ  ከሚያገኘው ገቢ በቦንድ ሳምንቱ ስኬት የአንድ ሺህ ብር ቦንድ መግዛቱን የገለጸው ደግሞ ሌላው የወረዳ ነዋሪ አዱኛ በዳዳ ነው፡፡

የግድቡ ግንባታ አስኪጠናቀቅ የቦንድ ግዥ በመፈጸም ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግሯል።

ወይዘሮ ግሹ አደሬ በበኩላቸው፤  ታላቁ የህዳሴ ግድብ  ኢትዮጵያዊያን ከድህነት ለመውጣት ተስፋ አድርገን በተባበረ አቅም እየገነባነው እንገኛለን ብለዋል፡፡

ግድቡን በራስ አቅም እየተሰራ እንዳለው ሁሉ ማንም በግንባታው ሂደትም ሆነ በውሀ ሙሌቱ ጣልቃ እንዲገባብን አንፈቅድም ሲሉም ገልጸዋል።

የዞኑ የህዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ፀኃፊ አቶ ታምሩ ጋረደው እንዳስታወቁት፤ በባሌ ዞን  ባለፉት ሁለት ሳምንታት በተካሄደው የቦንድ ሽያጭ ሳምንት ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ የቦንድ ግዥ ተከናውኗል፡፡


ህብረተሰቡ የህዳሴው ግድብ የመጀመሪው ዙር  የውሃ ሙሌት በመከናወኑ ለግንባታው የሚያደርገው ድጋፍ ለመቀጠል መነሳሳቱን አመልክተው፤ በቦንድ ሳምንቱ ለመሰባበስ የታቀደውን የ6 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር የቦንድ ግዥ ለማሳካት ርብርብ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

በባሌ ዞን የተለያዩ ወረዳዎች እየተካሄደ በሚገኘው የቦንድ ሳምንት ወጣቶች፣ ነጋዴዎች፣ ባለሃብቶችና የመንግስት ሰራተኛች በንቃት እየተሰተፉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በቦንድ ሽያጭ ሳምንቱ የቦንድ አቅርቦት እጥረት እንዳይኖር በሁሉም ወረዳዎች ውስጥ በሚገኙ የኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ቅርንጫፍ ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንም  አስረድተዋል፡፡

በባሌ ዞን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ ከተጣለበት ጊዜ አንስቶ ከ213 ሚሊዮን ብር በላይ የቦንድ ግዥ በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች መፈጸሙን ከዞኑ የህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ምክር ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም