ለግድቡ ድጋፋችንን በማጠናከር የኢንጂነር ስመኘውን ህልም ከዳር ለማድረስ እንሰራለን .... የወላይታ ሶዶ ከተማና የሰሜን ሸዋ ዞን ነዋሪዎች

62
ሶዶ / ፍቼ ሀምሌ 22/2010 ለሕዳሴው ግድብ የጀመሩትን ድጋፍ በማጠናከር የኢንጂነር ስመኘው ህልምን ከዳር ለማድረስ ተግተው እንደሚሰሩ የወላይታ ሶዶ ከተማና በኦሮሚያ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን ነዋሪዎች ገለጹ። ነዋሪዎቹ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዋና ሥራ አስኪያጅ በነበሩት ኢንጂነር ስመኘው በቀለ ድንገተኛ ሞት ጥልቅ ሀዘን እንደተሰማቸውም ተናግረዋል። የኢንጂነሩ ሞት የማይታመንና ልብ የሚሰብር መሆኑን የገለጹት የሶዶ ከተማ ነዋሪዎች፣ አንድነትንና ልማትን ለማፍጠን ከመቼውም ጊዜ በላይ ቆርጠው በተነሱበት ወቅት የልማት አርበኛ የሆኑትን ኢንጂነር ስመኘውን በማጣታቸው በእጅጉ አዝነዋል። የሁሉም ኢትዮጵያዊ አሻራ ያረፈበትን የህዳሴ ግድብ ለማጠናቀቅ በሚደረገው ጥረት ነዋሪዎቹ የጀመሩትን ድጋፍ በማጠናከር የኢንጂነር ስመኘውን የዓመታት ህልም ከግብ ለማድረስ እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል። ነዋሪዎቹ እንዳሉት የአገሪቱን ዕድገት በማፋጠን የቀደመ ዝናዋን ለመመለስ እየተደረገ ባለው አገራዊ ጥረት ህዝብን በማነሳሳት ወደልማት ከማምጣት እንጻር የኢንጂነር ስመኘው ድርሻ የጎላ ነው። ኢንጂነር ስመኘው የልማት ጀግና በመሆናቸው ዛሬ በሞት ቢለዩም የሰሩት ታሪካዊ ሥራ ለዘላለም በኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ እንዲታወሱ የሚያደርጋቸው መሆኑን ተናግረዋል ፡፡ የአገር ሀብት የሆኑትን ኢንጂነር ስመኘው በማጣታቸው ሀዘናቸው ጥልቅ መሆኑን የገለጹት ነዋሪዎቹ የእርሳቸውን ታሪክ በማስቀጠል ግድቡ ከፍጻሜ ለማድረስ ዝግጁነታቸውን አረጋግጠዋል። በተመሳሳይ ዜና በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የሚገኙ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችና የሥራ ኃላፊዎች በኢንጂነር ስመኘው በቀለ ድንገተኛ ሞት የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን ገልጸዋል። በኢንጂነሩ ፊትአውራሪነት የተጀመረው የህዳሴ ግድብ እስኪጠናቀቅ ድረስ የበኩላቸውን ድጋፍ በማድረግ የድርሻቸውን እንደሚወጡም አረጋግጠዋል። በኦሮሚያ ክልል ፍቼ ከተማ በተዘጋጀው የሃዘን መግለጫ ስነ-ስርዓት ላይ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችና የሥራ ኃላፊዎቹ እንዳሉት ኢንጂነር ስመኘው በቀለ የአገሪቱ የልማት አርበኛ ናቸው። ለዓመታት በበርሃ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ አገሪቱን ከድህነትና ኋላቀርነት ለማላቀቅ ሲሰሩ የቆዩ ታላቅ የአገር ባለውለታ መሆናቸውን ተናግረዋል ። የህዳሴውን ግድብ ከፍፃሜ በማድረስ የልማት አረበኛውን ራዕይ ለማሳካት በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ የገለጹት የህብረተሰብ ክፍሎቹ፣ ኢንጂነሩ ለአገር ባበረከቱት አስተዋጽኦ ስማቸው ህያው ሆኖ እንደሚቆይ ገልጸዋል። የህዳሴ ግድብ ግንባታ ከፍፃሜ እንዲደርስ ከሚያደርጉት ያልተቆጠበ ድጋፍ በተጨማሪ ለመልካም አስተዳደርና ለህብረተሰቡ ኑሮ መሻሻል  ከመንግስት ጎን ተሰልፈው እንደሚሰሩም ቃል ገብተዋል። ኢንጂነር ስመኘው የታገሉለት ዓላማ ፍሬ አፍርቶ ህዝቡ የልማት ተጠቃሚ እንዲሆን ምኞታቸው መሆኑን የተናገሩት የሁለቱ ከተማ ነዋሪዎች የአሟሟታቸው ሁኔታ በአፋጣኝ ተጣርቶ ለህዝብ ይፋ እንዲደረግና ተገቢ ፍትህ እንዲሰጥ ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም