በባሌ ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ ላይ የተከሰተን የእሳት ቃጠሎ ለመቆጣጠር ጥረት እየተደረገ ነው-ፓርኩ

82

መጋቢት 22/2013 (ኢዜአ) በባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ የተከሰተውን የእሳት ቃጠሎ ለመቆጣጠር ጥረት እየተደረገ መሆኑን የፓርኩ ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ሻሚል ከድር ለኢዜአ እንደገለጹት ካለፈው ሶስት ቀን ጀምሮ በፓርኩ የተቀሰቀሰውን የእሳት ቃጠሎ ለመቆጣጠር ጥረት እየተደረገ ነው።

ቃጠሎው የተከሰተው በባሌ ዞን ጎባና በምዕራብ አርሲ አዳባ ወረዳዎች በሚገኙ የፓርኩ ይዞታዎች ውስጥ ነው፡፡

በጎባ ወረዳ “ሀንገሶ” እና “ሼደም” እንዲሁም በአዳባ ወረዳ ደግሞ “ቡቻ ራያ” እና “ዌጌ” በሚባሉ ቀበሌዎች አዋሳኝ የፓርኩ ይዞታዎች ውስጥ መሆኑም ታውቋል፡፡ 

ባለፉት ሶስት ቀናት በቀላሉና በፍጥነት በሚቀጣጠሉ አስታ የተባሉ የዛፍ ቁጥቋጦ ዝርያዎች በተሸፈኑ አካባቢዎች የተነሳው ቃጠሎ በመሬት እየተዳፈነ ተመልሶ ስለሚቀሰቀስ የመቆጣጠር ስራውን አስቸጋሪ እንዳደረገው ተናግረዋል፡፡

ቃጠሎው ወደ ዋናው የፓርኩ የደን አካል እንዳይዛመትም በህብረተሰቡና በባለድርሻ አካላት ትብብር የመቆጣጠር ሰራው እየተካሄደ መሆኑን አስታውቀዋል ።

የአደጋው መንስዔ እየተጣራ መሆኑን የተናገሩት ሃላፊው ለቃጠሎው ምክንያት ይሆናሉ ተብለው የተጠረጠሩ  ሰባት  ግለሰቦች  በፖሊስ ቁጥጥር ሥር መዋላቸውን አመልክተዋል፡፡ 

በቃጠሎው የደረሰን የጉዳት መጠን ለጊዜው ለማወቅ አለመቻሉን ተናግረዋል ።

በ1962 ዓ.ም የተቋቋመው የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ፣ ጠቅላላ ስፋቱ ከ2 ሺህ 200 ካሬ ኪሎ ሜትር በላይ ሲሆን፣ ከባሕር ጠለል በላይ ከ1 ሺህ 500 እስከ 4 ሺህ 377 ጫማ የሚለካ ከፍታ ያለው የተፈጥሮ ፀጋ ነው፡፡

ብሔራዊ ፓርኩ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በዓለም ቅርስነት ጊዜያዊ መዝገብ ውስጥ ከመካተቱም በተጨማሪ፣ እጅግ ከፍተኛ የሆነ ብዝኃ ሕይወት ያለው በመሆኑ በዓለም 34ኛው በጣም ጥበቃ የሚያስፈልገው የብዝኃ ሕይወት (ሴንሲቲቭ ባዮዳይቨርሲቲ) አካባቢ መሆኑም ከፓርኩ ጽህፈት ቤት የተገኘ መረጃ  አመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም